የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሪፖርት እና የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት እየተካሄደ ይገኛል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዓመት አፈፃጰም ግምገማ እና የ2011 የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት በጁፒተር ሆቴል በመከናወን ላይ ይገኛል።

መርሐ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዝዳንት እና የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዐወል አብዱራሂም (ኮ/ል) የዘንድሮው ውድድር በስኬት ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ” በዘንድሮው ውድድር ላይ ትኩረት የምናደርገው የመርሐ ግብር መቆራረጥን ማስወገድ፣ ውድድሩ ግልፅ እና ፍትሀዊ እንዲሆን ማድረግ፣ ከክለቦች የሚመጡ አቤቱታዎችን በአግባቡ እና በወቅቱ ምላሽ መስጠት እና የክረምት ወራት ከመግባቱ በፊት ማጠናቀቅ ናቸው” ያሉት ኮ/ል ዐወል በሴቶች እግርኳስ እየታየ የሚገኘው የቡድን ማፍረስ አዝማሚያ ሊቆም ኤንደሚገባው ተናግረዋል።

” በክለቦች በኩል ጥሩ አዝማሚያ እየተመለከትን አይደለም። ሊጉ በ2004 ሲጀመር የሴቶች እግርኳስ ደረጃ በደረጃ ልክ እንደወንዶች በመላ ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ታስቦ ነበር። ሆኖም እየተሰጠው ያለው ትኩረት ዝቅተኛ ነው። ይህንን አዝማምያም በአስቸኳይ ለመቅረፍ እየሰራን ነው። እኛ የወንድ እግርኳስን ለመምራት ብቻ አይደለም የተቀመጥነው፤ የሴቶች እግርኳስም እንዲጎለብት እንሰራለን። ክለቦችም የሴቶች ቡድን ለማቋቋም በግዴታ ሳይሆን ከውስጣዊ ፍላጎት በመነጨ መሆን ይኖርበታል። የወንድ ስላለ የሴትም ይኑር ከሚል ብቻ መሆን የለበትም። በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ እያደገ ነው፤ ታድያ የእግርኳስን የወንዶች ብቻ ያደረገው ማነው። ተባብረን ይህን ግንዛቤ እጥረት መቅረፍ ይኖርብናል። ፌዴሬሽኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት ይሰራል።

” በመጨረሻም ለስፖርታዊ ጨዋነት ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ለመግለፅ እወዳለው። በውድድር ሂደት የሚገጥማችሁን ችግር ለመመልከት እና እናንተን ለማስተናገድ ፅህፈት ቤቱ ዝግጁ ነው። ዘንድሮ እንደከዚህ ቀደሙ እንግልት እና መጓተት አይኖርም።” ብለዋል።

ከምክትል ፕሬዝዳንቱ የመክፈቻ ንግግር በኋላ የ2010 የአፈፃፀም ሪፖርት በውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከበደ ወርቁ አማካኝነት ቀርቧል። የሁለቱ ዲቪዚዮኖች የውድድር ሒደት እና ቁጥራዊ መረጃዎች እንዲሁም ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች የሪፖርቱ አካል ሲሆኑ የዲሲፕሊን፣ የዳኞች እና የፀጥታ ኮሚቴ ሪፖርቶች በፅሁፍ ለታዳሚው ቀርቧል።

ከሪፖርቱ በመቀጠል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል። ተሳታፊዎችም አስተያየት እና ጥያቄያቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።