ደደቢት የአራት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀቀ

የዝውውር አካሄዱ መቀየሩን ተከትሎ ከታዳጊ ቡድኑ ተጫዋቾች በማሳደግ እና በዝቅተኛ ደሞዝ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ደደቢት አሌክሳንደር ዓወት ፣ ሙሉጌታ ብርሃነ ፣ ረሺድ ማታውሲ እና ሐድሽ በርኸን አስፈርሟል።

በትግራይ ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት የውድድሩ ኮከብ ተብሎ የተሸለመው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ረሺድ ማታውሲ የሰማያዊዎቹን ግብ ለመጠበቅ ለቀጣዩ አንድ ዓመት ከክለቡ ጋር ለመቆየት ተስማምቷል። ሌላው የደደቢት ፈራሚ ወጣቱ አጥቂ አሌክሳንደር ዓወት ሲሆን እሱም በተመሳሳይ ለቀጣይ አንድ ዓመት ከክለቡ ጋር ለመቆየት ተስማምቷል። በ2009 ከወጣቶች አካዳሚ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ባለፈው የውድድር ዓመት የተጫወተው አሌክሳንደር ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ ያገዙ 11 ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ተጫዋቹ በ2009 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሽልማትንም መውሰድ ችሏል።

ግብ ጠባቂው ሐድሽ በርኸ ወደ አሳዳጊ ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር በማድረግ በአንድ ዓመት ውል ደደቢትን ተቀላቅሏል። ተጫዋቹ ከዚህ በፊት ለደደቢት ታዳጊ ቡድን እና ትግራይ ውሃ ስራ መጫወቱም ይታወሳል። አራተኛው የደደቢት ፈራሚ የአጥቂ ክፍል ተጫዋቹ ሙሉጌታ ብርሃነ ከዚ በፊት ለወልዋሎ እና አክሱም ከተማ የተጫወተ ሲሆን በ 2004 ወልዋሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያልፍ የውድድሩ ኮከብ ተብሎ መሸለሙ ይታወሳል።

በትግራይ ዋንጫ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየት ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ደደቢቶች በዝውውር መስኮቱ 8 ተጫዋቾች ሲያስፈርሙ 10 ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋል።