በዓምላክ ተሰማ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን አይመራም

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አህጉራዊ ውድድሮችን እየዳኘ የሚገኘው በዓምላክ ተሰማ በዘንድሮው የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን እንደማይመራ ታውቋል።

ከ2016 ጀምሮ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ጨዋታዎችን በመዳኘት ላይ የሚገኘው በዓምላክ ተሰማ አምና በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አል አህሊ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ 1-1 የተለያዩበትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ከመምራቱ በተጨማሪ በ2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ መሳተፉ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮም ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎችን (እስከ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ) ሲመራ ቆይቷል።  

ካፍ በዘንድሮ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የቫር (በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ዳኝት) ለመጠቀም በማሰብ ኤሊት ኤ የሚባሉ ዋና ዳኞቹን በመጥራት ስልጠና የሰጠ ሲሆን በዓምላክም ይህንኑ ስልጠና ለመከታተል ወደ ግብፅ አምርቶ የነበረ በመሆኑ የ2018 የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ) ከ አል አህሊ (ግብፅ) በደርሶ መልስ ከሚያደርጉት ጨዋታ አንደኛውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል ተብሎ ሰፊ ግምት ከተሰጣቸው ዳኞች መካከል አንዱ የነበረ ቢሆንም ይህ ዕድል ሳይሳካ እንደቀረ ተገልጿል። ስልጠናውን ተከታትሎም ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል። 

2018 የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታ ነገ አል አህሊ ከ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ መካከል ካይሮ ላይ የሚያደርጉትን ጨዋታ ጋምቢያዊው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ የሚመራው ይሆናል።