ባህር ዳር ከተማ የሁለት የውጪ ዜጎችን ዝውውር አጠናቋል 

አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ባህር ዳር ከተማ ከቀናት በፊት በተዘጋው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቁ ታውቀል።

ቡድኑ ወደ ሊጉ መግባቱን ካረጋገጠ በኋላ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ እየቀላቀለ ይገኛል። በዚህም መሰረት ከዚህ ቀደም ስምንት ተጫዋቾችን አስፈርሞ የነበረው ቡድኑ አሁን የሁለት ተጨዋቾቹን ዝውውር በማጠናቀቅ የቡድን ጥልቀቱን አስፍቷል። ከሁለቱ ተጨዋቾች የመጀመሪያው ቡድኑን የተቀላቀለው ተጨዋች አሌክስ አማዙ ነው። ይህ የተከላካይ መስመር ተጫዋች አምና በመጀመሪያው የውድድር ዓመት ከአርባምንጭ ጋር ሲጫወት የነበረ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ከአዞዎቹ ጋር በመለያየት ከሊጉ መራቁ ይታወሳል። በከፍተኛ ሊጉ የተለያዩ ጥምረቶችን ሲያስመለክቱን የነበሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሲጠቀሙበት የነበረው አሌክስን በማስፈረማቸው የተረጋጋ የተከላካይ መስመር ጥምረት ያስመለክታሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

ሁለተኛው የቡድኑ ፈራሚ የአጥቂ መስመር ተጨዋቹ አህመድ ዋቴራ ነው። ይህ አይቮሪኮስታዊ አጥቂ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተቀይሮ እየገባ ሲጫወት የተስተዋለ ሲሆን ከሌላው አዲስ ፈራሚ ዳኮ አራፋት ጋር የአጥቂ መስመሩን እንደሚያጠናክር ታምኖበታል። 

የሁለቱን ዝውውር ማጠናቀቁን ተከትሎ በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ የውጪ ዜጎች ቁጥር አራት ያደረገሰው ባህር ዳር ከዚህ ቀደም ሀሪስተን ሄሱን እና አስናቀ ሞገስን ከኢትዮጵያ ቡና፣ ኤልያስ አህመድን ከሰበታ ከተማ ፣ ታዲዎስ ወልዴ እና ጃኮ አራፋትን ከወላይታ ድቻ፣ ማራኪ ወርቁን ከመከላከያ፣ እንዳለ ደባልቄን ከጅማ አባ ጅፋር ማስፈረሙ ሲታወስ የ13 ነባር ተጨዋቾችንም ውል ማደሱ ይታወቃል።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ