ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የሊጉን መክፈቻ ጨዋታ በድል ተወጥቷል

የ2011 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ሲጀመር ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ሲዳማ ቡና አዲስ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ግርማ በቀለ፣ ዳዊት ተፈራ እና ዳግም ንጉሴ በመጀመርያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ ሲገቡ በፋሲል ከነማ በኩል ሙጂብ ቃሲም፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ከድር ኩሊባሊ፣ ሽመክት ጉግሳ እና ኢዙ አዙካ አዲስ ከፈረሙት መካከል በመጀመርያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ የገቡ ናቸው። 


በርካታ የባለሜዳው ሲዳማ ቡና እንዲሁም ረጅም ርቀትን አቋርጠው በመጡ የፋሲል ደጋፊዎች ደማቅ ድጋፍ የታጀበው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች በመስመር በኩል ማጥቃትን ምርጫቸው ሲያደርጉ ፋሲሎች በአንፃሩ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሞክረዋል። ሙከራ ለማስተናገድ 19 ደቂቃዎችን በጠበቀው በዚህ ጨዋታ ዮሴፍ ዮሀንስ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የላካትን ኳስ አዲስ ግደይ ሞክሯት የግቡን ብረት ታካ የወጣችበት ቅፅበት የመጀመሪያ ሙከራ ሆናለች። 

ጨዋታው ቀስ በቀስ የኃይል አጨዋወት ሲታይበት 24ኛው ደቂቃ ላይም ሙጂብ ቃሲም በአዲስ ግደይ ላይ በሰራው ያልተገባ አጨዋወት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የመጀመርያው ጎል ተመዝግቧል። በ27ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በቀኝ መስመር በኩል ገፍቶ በመግባት የላከለትን ኳስ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ወደ ወላይታ ድቻ በውሰት ተሰጥቶ የነበረው ፀጋዬ ባልቻ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።


ሲዳማ ቡናዎች ከጎሉ መቆጠር በኋላም ተጨማሪ ጎሎች ጥረት ሲያደርጉ የአሰልጣኝ ውበቱ ፋሲል በተለይ በኤፍሬም ዓለሙ ላይ የተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሙከራ አድርገዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዓለሙ የፈጠራትን መልካም አጋጣሚ አዲሱ ናይጄሪያዊ አጥቂ ኢዙካ ኢዙ አግኝቷት ሳይጠቀምባት ቀርቷል። 45ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኬ በረጅሙ የለጋውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ አግኝቶ የግቡ ብረት የመለሰበትም ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። በሲዳማ በኩል ደግሞ አዲስ ግደይ የፈጠረለትና ፀጋዬ ባልቻ አግኝቷት ሳይጠበቀምበት የቀረው እድል ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው በፊት የተመለከትናቸው ናቸው።

የተደራጀ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባልታየበት በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተጫዋች ለውጦችን በተለይ በአጥቂ ስፍራ ላይ በመፈፀም ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ውጤት ለማስጠበቅ አፈግፍጎ በመከላከል የመልሶ ማጥቃትን የመረጡት ቡናዎቹ በሁለቱ መስመሮች የሚገኙት ሐብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ የግራ እና ቀኝ መስመሮች ላይ ትኩረት አድርገው ተጫውተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚን ገጭቶ የወጣበት እና አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ሞክሮ መሳይ አያኖ ያከሸፈበት ሙከራ በፋሲል በኩል አቻ ለመሆን የተቃረቡባቸው ሙከራዎች ሲሆኑ ሐብታሙ ገዛኸኝ በግል ብቃቱ ታግዞ ወደ ሳጥን ገብቶ የሞከራት ኳስ ለጥቂት የወጣችበት ደግሞ የሲዳማ ቡናን መሪነት ልታሰፋ የምትችል አድል ነበረች።

በ60ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ዮሴፍ ዮሀንስ በረጅሙ የላከለትን ኳስ ልማደኛው አዲስ ግደይ ከቀኝ መስመር እየገፋ ገብቶ የሚካኤል ሳማኪን አቅጣጫ በማሳት ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ የሲዳማን መሪነት ማስፋት ችሏል። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ሳማኬ ከግብ ክልሉ በረጅሙ የለጋውን ኳስ አዲሱ ናይጄሪያዊ አጥቂ ኢዙካ ኢዙ የሲዳማ ቡናን የተከላካይ እና ግብ ጠባቂን ያለመናበብ ተጠቅሞ ባገኛት መልካም አጋጣሚ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል።

የሊጉ መክፈቻ ጨዋታ በዚህ መልኩ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀንም ከሲዳማ ቡና ለ5፣ ከፋሲል ከነማ ደግሞ ለ3 ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ መዘዋል። 

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | LINK



ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ