የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 2-1 ፋሲል ከነማ

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ በ09፡00 ሀዋሳ ላይ ተካሂዶ ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን 2-1 መርታት ችሏል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ከዚህም በላይ ጎሎችን አስቆጥረን ማሸነፍ ይገባን ነበር” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

ስለጨዋታው…

“ውጤቱ ጥሩ ነው። በመጀመሪያ ጨዋታ በድል መጀመር ለኛ ትልቅ ነገር ነው። በደጋፊያችን ፊት በመጫወታችንም ተጋጣሚያችን ፋሲልም እንደ ስብስብም ሆነ እንደ ቡድን ጠንካራ ስለሆነ በማሸነፋችን በጣም ደስ ብሎኛል። ከዚህም በላይ ጎሎችን አስቆጥረን ማሸነፍ ይገባን ነበር። ምክንያቱም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ብዙ ጎል ጋርም ደርሰናል ፤ አልተጠቀምንም እንጂ። ስለዚህም ሦስት ነጥቡ ይገባናል።”

ስለ ተከላካይ ክፍላቸው ስህተት…

“ወደ 20ኛው ወይም 30ኛው ደቂቃ አካባቢ ተከላካይ መስመራችን ላይ የአቋቋም ችግር ነበር። ሰንደይ ሙቱኩ ባለመኖሩ ለውጦች ነበሩ። ከዛ ግን ግርማን ወደ ኋላ መልሰን ማስተካከያ አድርገናል ፤ የተከላካይ መስመራችንም ተረጋግቷል። በዛን ወቅት ፋሲሎች ኳስ በቋሚ ተመልሶባቸዋል። ያ ኳስ ቢገባ ዋጋ ልንከፍል እንችል ነበር።”

ስለ ፊት መስመራቸው…

“ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ የዛሬው የፀጋዬ ባልቻ የዛሬ እንቅስቃሴ  በጣም ጥሩ ነበር። በቦታው መሀመድ ናስርንም አስፈርመናል። በአጥቂ ክፍላችን ላይ ያን ያህል የሚይንሰጋ ክፍተትም የለብንም ብዬ ነው የማስበው።”


” ሽንፈቱ ይገባናል ማለት ይከብደኛል ፤ ቢያንስ ነጥብ መጋራት እንችል ነበር ” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
ስለ ጨዋታው…

“ይሄን ጨምሮ ቀጣዮቹ ሦስት አራት ጨዋታዎች ሊያስቸግሩን እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ነው የመጣነው ፤ ጥንቃቄ አድርገን ለመጫወት ሙከራ አድርገናል ብዙ ዕድሎችንም መፍጠር ችለናል። ተጋጣሚያችን ሲዳማዎች በጣም ጠንካራ ነበሩ። ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀምም ከኛ የተሻሉ ነበሩ። በመልሶ ማጥቃት ፣ በቅጣት ምት እና በማዓዘን ምት ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩም አይቻለው ፤ በዛ በኩል የተሻሉ ነበሩ። ከዛ በተረፈ ግን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የጎል ዕድሎች እንደመፍጠራችን ጨዋታውን መቆጣጠር እንችል ነበር። ቀድሞ ግብ ስለተቆጠረብን ነገሮች ቀላል አልሆኑልንም። እንደመጀመሪያ ጨዋታ ግን መጥፎ አይደለም።”

ስለ ሽንፈቱ…

” ሽንፈቱ ይገባናል ማለት ይከብደኛል ፤ ቢያንስ ነጥብ መጋራት እንችል ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ከፈጠርናቸው ዕድሎች በተጨማሪ ሁለተኛውም ግብ ከመቆጠሩ አስር ሰከንዶች ያህል በፊት ራሱ የሞከርነው ኳስ ከመስመር ላይ ነበር የወጣው። ዞሮ ዞሮ ብዙ ያገባ ነው የሚያሸንፈው። ጥረታችን እና ያሳየነው እንቅስቃሴ ግን መጥፎ አልነበረም።”

ስለአጥቂዎቻቸው…

“በአካል ብቃቱ ተዳክመዋል ማለት አልችልም። ዕድልን መጠቀም ላይ ነው ክፍተት የነበረው። ኳስ ስንጀምር ጥሩ ነበርን ስንመሰርትም እንደ ጀማሪ ቡድን መጥፎ አልነበርንም የግብ ዕድል መፍጠርም ላይም አልተቸገርንም ችግሩ ከተፈጠሩት ዕድሎች መሀል የተወሰኑትን እንኳን ወደ ግብ አለመቀየራችን ነው። እዛ ላይ መስራት እንዳለብን ነው ያየሁት።”


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ