ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ የዕለቱን ትልቅ ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን አስተናግዶ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 በመርታት የዓመቱን ጉዞ በድል ከፍቷል፡፡ 

በክረምቱ ዝውውር መስኮት ከፈረሙ ተጫዋቾች ውስጥ በዋሳ ከተማ በኩል ቡድኑን በአምበልነት የመራው አዳነ ግርማ የተሰለፈ ሲሆን አስራት መገርሳ ፣ ብርሀኑ ቦጋለ ፣ አማኑኤል ጎበና ፣ ደስታ ደሙ እና ዳዊት ፍቃዱ ደግሞ ጨዋታውን የጀመሩ የወልዋሎ አዳዲስ ተጫዋቾች ነበሩ።


የወልዋሎው አጥቂ ሪችሞንድ አዶንዶ ከቁምጣው ውስጥ ባደረገው የተለየ ትጥቅ እንዲሁም ለግብ ጠባቂው ዮሀንስ ሽኩር የህክምና ዕርዳታ በማስፈለጉ ጨዋታው ዘግየት ብሎ የጀመረ ነበር። በአማካዮቹ አዳነ ግርማ እና ታፈሰ ሰለሞን እንቅስቃሴ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ በደስታ ዮሀንስ ድንቅ ብቃት ታግዞ በጨዋታው ፍፁም የሆነ ብልጫን ያሳየ ሲሆን ሪችሞንድ አዶንጎ ላይ የተመሰረተው የወልዋሎ የማጥቃት አማራጭ ስኬታማ መሆን ሳይችል ቀርቷል።              

14ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ልዩነት ሲፈጥር የነበረው ደስታ ዮሀንስ በግራ የወልዋሎ የግብ መስመር እየገፋ ገብቶ ያደረገው ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ደስታ 28ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ላደረገው ሌላ ሙከራም ኳስ አመቻችቶ የሰጠ ሲሆን የሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት በዛው ቀጥሎ የወትሮው የመሀል ሜዳ የበላይነት ያልተለያቸው ሀዋሳዎችን 44ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ አድርጓል። ግቧን በግንባር በመግጨት ያስቆጠረው የፊት አጥቂው እስራኤል እሸቱ ሲሆን ከመስመር ኳስ ያሻገረለት ደግሞ ደስታ ዮሃንስ ነበር። 

የመጀመሪያው አጋማሽ የወልዋሎዎች ብቸኛ ሙከራ 31ኛው ደቂቃ ላይ ኦዶንጎ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ በፈጠረው አጋጣሚ የተገኘ ሲሆን ሜንሳህ ሙከራውን ማዳን ችሏል። ቡድኑ ግብ ከተቆጠረበት በኋላ በጭማሪ ደቂቃ ምላሽ ለመስጠት በዋለልኝ ገብሬ ያደረገው ሙከራም ፍሬ ማፍራት አልቻለም።

በ47ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከመስመር ያሻማውን ኳስ ከእስራኤል ጀርባ በመግባት ደስታ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ሲቀይረው መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ያለው ሀይቆቹ ሁለተኛው አጋማሽም በወጥነት ብልጫ መውሰድ ችለዋል። 


ቡድኑ ቀይሮ ወደ ሜዳ ያስገባቸው ወጣቶቹ አጥቂዎች ቸርነት አውሽ እና ብሩክ በየነ ተፅዕኖም ለሀዋሳ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን መፍጠር ችሏል። 86ኛው ደቂቃ ላይ ከሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት ተገኝቶ ቸርነት የሞከረው እና ዮሃንስ ሽኩር ያወጣው ኳስ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ነው። ነገር ግን ጭማሪ ደቂቃ ላይ ኮከብ ሆኖ ያመሸው ደስታ ዮሃንስ ከመሀል የላከውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን በአግባቡ ተቆጣጥሮ እና ሁለት የወልዋሎ ተከላካዮችን አልፎ ግብ ጠባቂው ዮሀንስ ሽኩርን አቅጣጫ በማሳት በድንቅ አጨራረስ ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በዕለቱ ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አምስት የቢጫ ካርዶች የተመዘዙበት ፣ በርካታ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች እና ረጅም ርቀት አቋርጠው የመጡ የወልዋሎ ደጋፊዎች የታደሙበት ጨዋታም በሀዋሳ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | LINK


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ