ከነዓን ማርክነህ በአዳማ ለተጨማሪ ዓመት ይቆያል

በ2010 የውድድር ዘመን ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ከነዓን ማርክነህ በአዳማ ከተማ ለተጨማሪ ዓመት የሚያቆየውን ውል አራዘመ።

የአዳማ ከተማው የአማካይ አጥቂ ስፍራ ተጫዋች ከነዓን በውድድር ዓመቱ በአጠቃላይ 8 ጎሎች ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበልም የተሳካ የውድድር ጊዜ አሳልፏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት ከመጠራቱ ባሻገርም ለሳምንታት ያህል ወደ ሰርቢያ በማቅናት የሙከራ ጊዜ አሳልፎ ተመልሷል። ይህን ወቅታዊ ብቃቱን መነሻ በማድረግ የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረም ይታወሳል።

ከነዓን ምንም እንኳን ከአዳማ ጋር የሚያቆየው ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ቢኖረውም ከሚከፈለው ወርሃዊ ደሞዝ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከአዳማ ጋር በስምምነት በመለያይት የተሻለ ተጠቃሚ ወደሚሆንበት ክለብ ያመራል ተብሎ ሲጠበቅ ዛሬ ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋገር ወርሃዊ ደሞዙ ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ ተደርጎለት የአንድ ዓመት ተጨማሪ ኮንትራት በማራዘም ለቀጣይ ለሁለት ዓመታት (እስከ 2012 መጨረሻ) በአዳማ የሚያቆየውን ውል አራዝሟል።

የአዳማ ተስፋ ቡድን መነሻውን ያደረገው ከነዓን ለሁለት ዓመታት በከፍተኛ ሊግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በአዲስ አባባ ከተማ በመጫወት ነበር በ2010 የውድድር ዘመን ወደ አዳማ ከተማ ያመራው።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ውላቸውን ለማራዘም የግድ እስከ ኮንትራታቸው ፍፃሜ የመጠበቅ ልማድ የነበረ ሲሆን አሁን አሁን ክለቦቻችን ተጫዋቾቻቸው ኮንትራት እያላቸው ደሞዛቸውን በማሻሻል ሲያራዝሙ እየታዩ ይገኛል።  የአዳማ ተሞክሮ ለብዙዎች እንደ ምሳሌ የሚቆጠር ነው።