በዋልያዎቹ ምክንያት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አይካሄዱም

በፕሪምየር ሊጉ ጥቅምት 30 እንደሚደረጉ ይጠበቁ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ በዋልያዎቹ የዝግጅት ጊዜ ምክንያት ተዘዋወረዋል።

የአንደኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎችን በማስተናገድ ያለፈው ሳምንት ጅማሮውን ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሁለተኛ ሳምንት መርሀ ግብሮቹ መካከል አምስቱ ረቡዕ ጥቅምት 30 እንደሚካሄዱ ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ዋልያዎቹ ኅዳር 09 ቀን በአዲስ አበባ ስታድየም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አምስተኛ ጨዋታቸውን ከጋና ጋር የሚያደርጉ በመሆኑ ለዝግጅት ሲባል የሊጉ መርሀ ግብር ማስተካከያ ተደርጎበታል።

ሁለቱ የሊግ ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ የተላለፉት የጋናውን ጨዋታ ተከትሎ ጥቅምት 26 ዋልያዎቹ ለዝግጅት የሚሰበሰቡ በመሆናቸው ነው። ከሶማልያ ጋር የሚደረገው የኦሎምፒክ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታም ለለውጡ ሌላኛው ምክንያት ሆኗል። በዚህም ምክንያት ከሁለት በላይ ተጫዋቾች ያስመረጡት ጅማ አባ ጅፋር ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ እንዲያደርጓቸው ይጠበቁ የነበሩት ጨዋታዎች የማይካሄዱ ይሆናል። ጨዋታዎቹም ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር መከላከያን የሚያስተናግድበት እና አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገናኙበት ናቸው።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች እና የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥቅምት 24 እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ከተካሄዱ በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታው ምክንያት እንደሚቋረጥ ይታወቃል። ሊጉ በሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከኅዳር 14 ጀምሮ እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።