ሪፖርት | መቐለ ወልዋሎን በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በሁለተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ አንድ ጨዋታ ትግራይ ስታድየም ላይ ተስተናግዶ መቐለ 70 እንደርታ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ሚካኤል ደስታ ከማዕዘን ምት በቀጥታ ባስቆጠራት ግሩም ግብ ታግዞ ወልዋሎን 2-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችሏል።

የወልዋሎ ስታድየም በእድሳት ላይ በመሆኑ የሜዳ ጨዋታቸውን በመቐለው ትግራይ ስታድየም እያከናወኑ የሚገኙትና ዛሬ ባለሜዳ የነበሩት ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፉበት ጨዋታ ስብስብ ዮሃንስ ሽኩርን የ6 ወራት ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ በተመለሰው በረከት አማረ ፣ ዳንኤል አድሓኖምን በእንየው ካሳሁን፣ ዳዊት ፍቃዱን በኤፍሬም አሻሞ ፣ ዋለልኝ ገብሬን በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ቀይረው ሲገቡ መቐለዎች በበኩላቸው ካለፈው ሳምንት ስብስባቸው አንተነህ ገ/ክርስቶስን በያሬድ ሀሰን ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስን በስዩም ተስፋዬ ፣ ዮናስ ገረመውን በያሬድ ከበደ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በደጋፊዎች ደማቅ ድባብ ታጅቦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ እና ምክትላቸው ዓወል አብዱራሂም የክብር እንግድነት በጀመረው ጨዋታ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወልዋሎዎች ከተጋጣምያቸው በተሻለ ጫና ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ የጎል ዕድሎችም ፈጥረዋል። በተለይም በመስመር በኩል በጥሩ የኳስ ፍሰት የመጣችው ኳስ አፈወርቅ ኃይሉ አግኝቶ ያልተጠቀመባት እና ብርሃኑ ቦጋለ ከሳጥን ጠርዝ አከባቢ አሻምቷት አሚን ነስሩ እንደምንም በግንባሩ ገጭቶ ያዳናት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ወልዋሎዎች በመቀባበያ መስመሮች የሚያደርጓቸው ጫና ፈጥሮ የመጫወትን ተቋቁመው እንደወትሮው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወት ያልቻሉት መቐለዎች በጨዋታው ያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በጥሩ ቅብብል ገብተው ወደ ግብ ከመሞከራቸው በፊት ብርሃኑ ቦጋለ ካስጣላት ሙከራ ውጭ ለጎል የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ቢቆዩም በ33ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። አምበሉ ሚካኤል ደስታ በቀጥታ ከማዕዝን ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ መቐለ ጨዋታውን አንድ ለባዶ እንዲመራ አስችሏል።

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች አጥቅተው የተጫወቱት ወልዋሎዎች በርከት ያሉ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም አማኑኤል ጎበና በግሩም ሁኔታ ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ እንየው ካሳሁን ያመከናት ኳስ በወልዋሎ በኩል የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች።


ሐይደር ሸረፋ ከርቀት መቶ በረከት አማረ በቀላሉ ባዳነበት ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም መለኪያዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። በዚህ ክፍለ ጊዜ የመጀመርያዎቹ 5 ደቂቃዎች ከመቐለ በተሻለ ኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ወልዋሎዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሪችሞንድ አዶንጎ በ 50′ ደቂቃ ላይ ከመስመር የተላከችለትን ኳስ ተጠቅሞ ከ ፍሊፔ ኦቮኖ አንድ ለ አንድ ቢገናኝም ኦቮኖ በልዩ ብቃት አድኗታል።

መቐለ 70 እንደርታ በሁለተኛው አጋማሽ ከጥብቅ መከላከሉ ባሻገር ሁነኛ የመልሶ ማጥቃት ዕድል ሳያገኙ ቢቆዩም ከ 60ኛው ደቂቃ በኋላ ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ፈጥረው ነበር። በዚህ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል የፈጠሩት ተግባቦት ለወልዋሎ ተከላካዮች ፈተና ሆኖ ነበር። በ66ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ቀስ በቀስ ያንሰራሩት መቐለዎች ሳሙኤል ሳሊሶ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ በግሩም አጨራረስ ባስቆጠራት ጎል ተጠቅመው ሁለት ለባዶ መምራት ችለዋል።

 

ከሳሙኤል ጎል በኋላ ተከላካዩ አቼምፖንግ አሞስን በአጥቂ መስመር ላይ ቀይረው ያስገቡት መቐለዎች አፈግፍገው ሲጫወቱ በአንፃሩ ወልዋሎች አጥቅተው ቢጫወቱም ብርሃኑ ቦጋለ ከቅጣት ምት ከሞከራት አስቆጪ ሙከራ ውጭ የግብ እድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው በመቐለ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ሁለቱ ቡድኖች በ2005 አርገውት ሶስት ለ ሁለት ካለቀው ጨዋታ በኋላ አሸናፊው ቡድን ከአንድ ጎል በላይ አስቆጥሮ ያሸነፈበት የመጀመርያው ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል።

ጨዋታውን የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ 6 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዟል።

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | LINK