የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዛሬ ተጀመረ

ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የሚደረገው የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የአቋም መፈተሻ ውድድር ዛሬ በዱራሜ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በደቡብ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን አስተናጋጅነት በካስቴል ቢራ ስፖንሰር አድራጊነት በየዓመቱ የሚደረገው ይህ ውድድር አስቀድሞ ከጥቅምት 18 ጀምሮ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በክለቦች የዝግጅት ጊዜ እጥረት ምክንያት ቀኑ ተገፍቶ ዛሬ ጅማሮውን አድርጓል። በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ከ10 በላይ ሲሆኑ ሁሉንም ተሳታፊ ያደርጋል ቢባልም ክለቦቹ ባነሱት የዝግጅት ጊዜ እጥረት እና የፋይናንስ እጥረት ክለቦቹ በርክተው በውድድሩ ተካፋይ እንዳይሆኑ እንዳደረገ የደቡብ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። 

በዚህም መሰረት ውድድሩ በስምንት ክለቦች መካከል ሲደረግ ዛሬ 9:00 በተደረገ የመክፈቻ ጨዋታ ከሊጉ የወረደው አርባምንጭ ከተማን ከአስተናጋጁ ዱራሜ የተገኘው ሀምበሪቾ ጋር ተገናኝተው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀዋል። በ46ኛው ደቂቃ በረከት ቦጋለ ለአርባምንጭ ከተማ 76ኛው ደቂቃ ላይ ቴዲ ታደሰ ለሀምበሪቾ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። 

በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ሀምበሪቾ ዱራሜ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ስልጤ ወራቤ፣ ከምባታ ሺንሺቾ፣ ሀላባ ከተማ፣ ሶዶ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ከአንደኛ ሊግ ደግሞ ኮንሶ ኒውዮርክ ሲሆኑ ውድድሩ እስከ ህዳር 4 የሚዘልቅ ይሆናል።

በ2010 ሆሳዕና ላይ በተካሄደው ውድድር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ደቡብ ፖሊስ ሀዲያ ሆሳዕናን በማሸነፍ ቻምፒዮን መሆኑ አይዘነጋም፡፡