ሪፖርት | መከላከያ ደቡብ ፖሊስን በመርታት ሊጉን በድል ጀምሯል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ተሰተካካይ ጨዋታ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ደቡብ ፖሊስን ከመከላከያ አገናኝቶ በጦሩ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ከአምናው የከፍተኛ ሊግ ተሳትፏቸው ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል ደስታ ጊቻሞ ፣ ብሩክ ኤልያስ እና ብርሀኑ በቀለን ብቻ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲያስገቡ የተቀሩት ስምንት ተጫዋቾች ግን አዲስ ፈራሚዎች ነበሩ። መከላከያ ከቀናት በፊት ጅማ አባ ጅፋርን በአሸናፊዎች አሸናፊ ሲረታ ከተጠቀመበት አሰላለፍ አለምነህ ግርማን በታፈሰ ሰርካ ፣ ለኦሎምፒክ ቡድኑ የተጠራው ቴዎድሮስ ታፈሰን ደግሞ በበሀይሉ ግርማ ተክቷል። ጨዋታው በደቡብ ክልል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ልዩ አድማቂነት በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ በዕለቱ ዋና ዳኛ ሳህሉ ይርጋ አማካኝነት ከተያዘለት ደቂቃ 10 ያህል ዘግይቶ 9:10 ላይ ጀምሯል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አስር ደቂቃወች ፍፁም የባለ ሜዳው ደቡብ ፖሊስ የማጥቃት ሀይል አመዝኖ የታየባቸው እና የመከላከያ ጉልህ ያልሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን የተስተዋለባቸው ነበሩ። ፖሊሶች በተደራጀ የመስመር ላይ አጨዋወት በብሩክ ኤልያስ በመጠቀም ያለቀላቸውን ዕድሎች ለመፍጠር ጊዜ አልወሰደባቸውም። 3ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል የተገኘውን የቅጣት ምት አዲስ ፈራሚው መስፍን ኪዳኔ በቀጥታ መቶት አበበ ጥላሁን ከግቡ መስመር ላይ በግንባሩ ያወጣት ኳስ የባለሜዳዎቹ የመጀመሪያ ጠንካራ ሙከራ ነበር። በመከላከያዎች በኩል ደግሞ ፍሬው በግሉ ካደረገው ሙከራ በተጨማሪ ከቅጣት እና ከማዕዘን ምት ለምንይሉ በፈጠራቸው አጋጣሚዎች የተደረጉ ሙከራዎች ይነሳሉ።

ደቡብ ፖሊሶች ብሩክ ኤልያስ በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን እየገባ በሚፈጥራቸው አጋጣሚዎች ይበልጥ ጫናቸው ቢጨምርም በቶሎ ግብ ለማግኘት ግን አልቻሉም። 16ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ይስሀቅ በሰጠው ኳስ ከግቡ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የጦሩ ተከላካይ አዲሱ ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ ተንሸራቶ ያወጣበት ፤ ከአስር ደቂቃ በኋላ ደግሞ በቀኝ በኩል መስፍን ኪዳኔ የሰጠውን ኳስ ወደ ሳጥን ገብቶ ሲመታ አቤል ማሞ በአስደናቂ ብቃት ያዳነበት ተጠቃሽ የብሩክ ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም 38ኛው ደቂቃ ላይ በመስፍን ኪዳኔ ተጨማሪ የቅጣት ምት ሙከራ ያደረጉት ባለሜዳዎቹ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ግብ አስቆጥረዋል። የቀድሞው ቡድኑን የገጠመው የተሻ ግዛው በቀኝ የመከላከያ የግብ ክልል እየገፋ ገብቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ የአቤል ማሞ መዘንጋት ታክሎበት ነበር ከመረብ ያረፈው።

ነገር ግን የደቡብ ፖሊሶች መሪነት ለአምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የዘለቀው። 29ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከዳዊት እስጢፋኖስ በተነሳ ኳስ በፍሬው ሰለሞን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት መከላከያዎች ከሽመልስ ተገኝ ሌላ ሙከራ በኋላ ወደ ግብ የደረሱበት አጋጣሚ ፍሬያማ ሆኗል። በ45ኛው ደቂቃ አቻነቷን ግብ ያስቆጠረው ምንይሉ ወንድሙ ሲሆን ጎሏ የተከላካዮች ስህተት እና የፍሬው ሰለሞን መልካም እይታ የታየባት ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የቀዘቀዘ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ሆኖም ቡድኖቹ ከመልበሻ ክፍል ከገቡ ሁለት ደቂቃዎች በኃላ በሀይሉ ግርማ እና ዳዊት እስጢፋኖስ በፈጠሩት አስደናቂ ቅብብል ከእረፍት መልስ ለመከላከያ ጥሩ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ፍሬው ሰለሞን ግብ አስቆጥሮ ጦሩን መሪ አድርጎል። የአቻነት ግብ ፍለጋ የአጥቂ ቁጥራቸውን የጨመሩት ደቡብ ፖሊሶች ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረግው ከሀረር ሲቲ የተገተኘው ልዑል ደረጀን አስገብተዋል። በመከላከያዎች በኩል ከእረፍት መልስ የዳዊት እስጢፋኖስ እና ፍሬው ሰለሞን በሳል እንቅስቃሴዎች ነበሩ ለውጤቱ ማማር ተጠቃሽ የነበሩት።

በሙከራ ደረጃ በሁለተኛው አጋማሽ ፍሬው ከተመስገን ገብረኪዳን ባገኘው ኳስ ሙከራ አድርጎ ዳዊት የያዘበት ከመከላከያ ፤ ልዑል ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች ደግሞ ከደቡብ ፖሊስ የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ 77ኛው ደቂቃ ላይ ልዑል ከግብ ጠባቂው አቤል ጋር ተገናኝቶ የመታት ኳስ በአቤል ማሞ ጥረት የዳነች ነበረች። የመጨረሻወቹ 15 ደቂቃዎች ግን አሰልቺ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያሳየን ነበር። የመከላከያ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ እየወደቁ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ባደረጉት ጥረት ከፍተኛ ተቃውሞን ያስተናገዱበት ጨዋታ በአልቢትሩ አምስት ቢጫ ካርዶች ተመዘውበት በመከላከያ 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል።

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ | LINK