ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀዋሳን ድል አድርጓል

በኢትዮጵያያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ጎንደር ፋሲለደስ ስታድየም ላይ በአወዛጋቢ የዳኛ ውሳኔ ለ20 ደቂቃዎች ለመቋረጥ በተገደደው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን  3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በመጀመሪያ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ስታድየም ሲዳማ ቡናን ገጥሞ 2-1 የተሸነፈው ፋሲል ዛሬ ኢዙ አዙካን በኤዲ ቤንጃሚን የተካ ሲሆን በሀዋሳ በኩል ደግሞ ወልዋሎ ዓ.ዩን 3-0 ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ኄኖክ ድልቢ እና እስራኤል እሸቱን በአስጨናቂ ሉቃስ እና ምንተስኖት አበራ ተለውጠዋል።


የመጀመሪያውን አጋማሽ  አጥቅተው መጫወት የመረጡት  ፋሲል ከነማዎች ገና በ2ኛው ደቂቃ ነበር በአብዱርሀማን ሙባረክ ሙከራ ወደ ሀዋሳ ከተማ ግብ ክልል መድረስ የጀመሩት። በመቀጠልም 7ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አለሙ ከግራ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክር ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ኳስ ሳሆሆ ሜንሳህ መልሶበታል። ሜንሳህ ተጨማሪ የሱራፌል ዳኛቸው እና ሰይድ ሁሴን ተሻጋሪ ኳሶችንም አውጥቷል። አምሳሉ ጥላሁን ከሰይድ በተሻገረ ሌላ ኳስ ለመሞከር ባደረገውም ጥረትም ግብ ጠባቂውን መቅደም ሳይችል ቀርቷል። 

ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ሀዋሳዎች በኩል 35ኛው ደቂቃ ላይ  ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ  አሻምቶት ሚካኤል ሳማኬ በቀላሉ ከያዘበት ኳስ ውጭ የተሻለ ሙከራ  አላደረጉም። የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ከመጠናቀቁ በፊት በተደጋጋሚ ሰዓት ለመግደል ሙከራ ሲያደርግ የነበረው ሶሆሆ ሜንሳህ የጨዋታውን የመጀመሪያ ቢጫ ካርድ አግኝቶም ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ መንፈስ የተመለሱት ፋሲል ከነማዎች የተሻለ ተጭነው በመጫወት 47ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከርቀት አክርሮ በመታው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ጫናቸውን ማሳደር ቀጥለዋል። 53ኛ ደቂቃ ላይም  ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ዉጭ የተገኝውን ኳስ ኤዲ ቤንጃሚን መሬት ለመሬት አክርሮ ስመታ ሶሆሆ ሜንሳህ ይዞ በመልቀቁ  ሙጅብ ቃሲም አጋጣሚውን ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ሆኖም ተጭነው የተጫወቱት ሀዋሳዎች ከ14 ደቂቃዎች በኋላ ምላሽ ሰጥተዋል። ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ገብረመስቀል ዱባለ በመልሶ ማጥቃት 67ኛ ደቂቃ ላይ  ከደስታ ዮሀንስ የተሻገረለትን ኳስ በማስቆጠር ነበር ሀዋሳን አቻ ያደረገው። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አጥቅተው የተጫወቱት ፋሲል ከነማዎች በ70ኛ ደቂቃ ኤዲ ቤንጃሚን በመልሶ ማጥቃት  ያገኝውን ኳስ ወደ ግብ አክርርሮ ሞክሮ የቀኝ ቋሚ ከመለሰበት በኋላ በያሬድ ባየ እና ሙጅብ ቃሲም ያደረጓቸው መከራዎችም ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።  

በዚህ መልኩ በአቻ ውጤት የቀጠለው ጨዋታው አወዛጋቢ ክስተት የተፈጠረው ወደ ማብቂያው ላይ ነበር። የዕለቱ ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ 87ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ኤፍሬም አለሙ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በማለት ፊሽካ ካሰማ በኋላ ሽመክት ጉግሳ ግብ በማስቆጠሩ ግቡን አፅድቋል። በውሳኔው ከሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ጋር በተፈጠረው አለመግባባትም ጨዋታዉ ከ20 ደቂቃ በላይ ተቋርጦ ቆይቶ በመጨረሻም የፍጹም ቅጣት ምቱ እንዲመታ ሆኗል። የፍፁም ቅጣት ምቱ በመሰጠቱም ከሀዋሳ ተጫዋቾች ጋር የተፈጠረው ግርግር አዳነ ግርማ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበትን ውሳኔ አስከትሏል። 

ከደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብነት በቀየረው የፍፁም ቅጣት ምት ተጀምሯል። ፋሲል ከነማዎች በድጋሚ መሪ ከሆኑ በኋላ የተሻለ ተጭነው በመጫወት 90ኛው ደቂቃ ላይ ከሽመክት ጉግሳ በተሻገረ ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን በ3-1 ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። በውጤቱም አፄዎቹ ከሽንፈት ያገገሙበትን ድል ሲያስመዘግቡ በሊጉ ታሪክ ሀዋሳን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፉበትን ውጤትም ነው ያሳኩት።

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ | LINK