ጅማ አባ ጅፋር የቴዎድሮስ ታደሰን ዝውውር አጠናቋል

በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ጅማ አባ ቡና ዓመቱን ያጠናቀቀው ቴዎድሮስ ታደሰ ወደ ሌላኛው የጅማ ክለብ በአንድ ዓመት ውል አምርቷል፡፡

ቁልፍ ተጫዋቾች አሳልፎ እየሰጠ የሚገኘው የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ጅማ አባ ቡና አሁን ደግሞ ሌላኛውን አጥቂውን አጥቷል። ጅማ አባ ቡና ምንም እንኳን ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከጫፍ ደርሶ በሽረ ተረቶ ዕቅዱ ቢደናቀፍም በክለቡ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ቴዎድሮስ ታደሰ ነበር። ቴዎድሮስ በ2010 የከፍተኛ ሊግ የውድድር ዓመት 12 ግቦች በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥም ችሎ ነበር።

የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊው ለሌላኛው የጅማ ክለብ ጅማ አባ ጅፋር የአንድ ዓመት ኮንትራት ፈርሟል፡፡ በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ጉዳት የገጠመው አዲሱ ፈራሚ ጋናዊው ቢስማርኪ አፒያን ቦታ መሸፈን ይጠበቅባቸው የነበሩት ሻምፒዮኖቹ ቴዎድሮስን ማስፈረማቸው በቦታው ያላቸውን አማራጭ እንደሚያበዛላቸው ይታመናል።