ከፍተኛ ሊግ: ለገጣፎ ዘጠኝ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ለገጣፎ ለገዳዲ የምክትል አሰልጣኝ ቅጥርን ጨምሮ የነባር ተጫዋቾቹን ውል የማራዘም እና አዳዲሶችንም የማስፈረም ስራ ሰርቷል።

በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ እየተመራ የከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ን በሦስተኝነት ያገባደደው ለገጣፎ ለገዳዲ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ኃላፊነቱን ለአሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ መስጠቱ ይታወሳል። ክለቡ በመቀጠል ደግሞ የ16 ተጫዋቾቹን ውል ሲያድስ አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመን በምክትልነት ለአንድ ዓመት መቅጠሩ ታውቋል። ከዚህ ውጪም ከስምንት የከፍተኛ ሊግ እና ከአንድ የአንደኛ ሊግ ክለቦች የተወጣጡ የዘጠኝ ተጨዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

ክለቡ ያስፈረማቸው ተጨዋቾች ሁሉንም የቡድኑን ክፍሎች ያማከሉ ናቸው። በዚህም መሰረት የሰንዳፋውን ግብ ጠባቂ ሚኪያስ ገቹን ሲያስፈርም ወንድምአገኝ ግርማን ከወልቂጤ ከተማ ነስረዲን ኃይሉን ደግሞ ከቡራዩ ከተማ በተከላካይ መስመሩ ላይ አካቷል። ከዚህ በተጫማሪ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች የሆኑት ሽመክት ግርማን ከአክሱም ከተማ ፣ አንዋር አብዱልጀባልን ከኢኮስኮ ፣ ዳዊት ተስፋዬን ከሱሉልታ ከተማ እና ፍቅሩን ከለገጣፎ 01 ማምጣት ችሏል። የአክሱም ከተማው ተዘራ ጌታቸው እና የነቀምት ከተማው አብርሀም ጫላ ደግሞ አዳዲሶቹ የለገጣፎ አጥቂዎች ሆነዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ አዳዲሶቹን ተጨዋቾች በአንድ ዓመት ውል ሲሆን ያስፈረመው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱንም ዝዋይ ላይ ሲያደርግ ቆይቶ ወደ ለገጣፎ መመለሱ ታውቋል።