አውስኮድ በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

በሃገሪቱ የሊግ እርከን ሁለተኛ በሆነው ከፍተኛ ሊግ ላይ እየተወዳደረ የሚገኘው አማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት (አውስኮድ) ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሮ የዝውውር እንቅስቃሴ እያደረገ እየሰራ ይገኛል።

ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ላይ ከአሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ ጋር ከተለያየ በኋላ የስራ ቅጥር ማስታወቂያ በማውጣት አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስን በማስፈረም የአዲሱን የውድድር አመት ስራ አንድ ብሎ የጀመረው ክለቡ በመቀጠል ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር በማዞር በአጠቃላይ በአራቱም የሜዳ ክፍሎች (ግብ ጠባቂ፣ ተከላካይ፣ አማካይ እና አጥቂ) የሚጫወቱ 17 አዳዲስ ተጨዋቾችን አስፈርሟል።

በዚህም መሰረት ደረጀ ዓአለሙ (ከወልዲያ ከተማ) ፣ አብዱልሀፊዝ መኪ (ከቤንች ማጂ ቡና) ፣ ልደቱ ጌታቹው እና አብዱራህዛቅ ናስርን (ከጅማ አባ ቡና)፣ አቤል ዓለሙን እና ሙክታር ሀሰን ( ከወሎ ኮምቦልቻ) ፣ ባለምላይ ሞትባይኖር (ከባህር ዳር ከተማ) ፣ ፍቃዱ ታደሰ (ከኢኮስኮ) ፣ ዓለሙ ብርሃኑ (ከቡራዩ ከተማ)፣ ውብሸት ባህሩን (ከኦሜድላ) ፣ ሰዒድ ሰጠኝ (ከአማራ ፖሊስ) ፣ ጅለይን ከማል (ከሀምብሪቾ)፣ ወንድማገኝ በለጠ (ከወላይታ ድቻ) ፣ ኤፋሬም ዘሪሁን (ከሻሸመኔ ከተማ) ፣ ሳሙኤል አባተ (ከጎጃም ደብረ ማርቆስ)፣ ተዘራ አቡቴ (ከሀድያ ሆሳዕና) እንዲሁም ታሪኩ ጎጀሌ (ከነቀምት ከተማ) ወደ ክለቡ ቀላቅሏል።

በአዲሱ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ፎርማት መሰረት በማዕከላዊ ዞን የተመደበው ቡድኑ በሚወዳደርበት ሊግ ተፎካካሪ ለመሆን ካስፈረማቸው ተጨዋቾች በተጨማሪ ይጠቅሙኛል ያላቸውን የ7 ነባር ተጨዋቾችንም ውል አራዝሟል። መልካሙ ዓለሙ ፣ ሰለሞን ጌዴዮን ፣ ይገርማል መኳንንት ፣ ኃብተገብርኤል ተስፋሁን፣ መላኩ ፈጠነ ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ሚካኤል ዳኛቸው ውል ያራዘሙ ተጫዋቾች ናቸው።

የክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ በቀጣይ ወር በሚጀምረው ውድድር አምና ወደ ከፋ ቡና ከማምራታቸው በፊት ያሰለጥኑት የነበረው ፌደራል ፖሊስን በመግጠም ዓመታዊ ውድድራቸውን ይጀምራሉ።