” ከካፍ ጋር በተለይም በሴቶች እግርኳስ ዙሪያ መስራት የሁልጊዜ ህልሜ ነበር ” አዲሷ የካፍ የሴቶች እግርኳስ ልማት ኃላፊ መስከረም ታደሰ 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፀሀፊ ወይዘሮ መስከረም ታደሰ በካፍ የሴቶች እግር ኳስ ልማት ኃላፊ በመሆን  ተሹማለች።

የቀድሞዋ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር መስከረም ታደሰ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከገባች በኃላ ያለፉትን አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ትልቅ ዕድገት እንዲመጣ እና የተለያዩ የልማት ስራዎች በአግባቡ እንዲሰሩ ከሚጥሩ ባለሙያዎች መካከል አንዷ ሆና ቆይታለች። በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ የሴቶች እግር ኳስ እንዲያድግ ካበረከተችው አስተዋፅኦ አንፃርም ካፍ የሴቶች እግር ኳስ ልማት ኃላፊ አድርጎ መርጧታል።

በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ምክትል ፀሀፊ በመሆን እየሰራች የምትገኘው መስከረም በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በቡድን መሪነት በመምራት እንዲሁም የሴካፋ የሴቶች ቻምፒዮና ላይም በፀሀፊነት እና በአስተባባሪነት ማገልገሏ ለቦታው ከፍተኛ ግምትን እንድታገኝ እንዳስቻላት ይታመናል። መስከረም ከዚህ ባለፈ በካፍ የሲምፖዚየም ኮሚቴ ውስጥ ገብታ ያለፉትን ጥቂት ወራት ስትሰራ ቆይታለች። 

ነገ በካይሮ ለሚደረገው የካፍ ስብሰባ በዝግጅት ላይ የምትገኘው መስከረም ጉዳዩን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራት አጭር ቆይታ ቀጣዮቹን አስተያየቶች ሰጥታለች።

ስለ ሹመቱ…. 

 ” እዚህ በመድረሴ ክብር ይሰማኛል ፤ ከካፍ ጋር በተለይም በሴቶች እግርኳስ ዙሪያ መስራት የሁል ጊዜ ህልሜ ነበር። እንዳማስበው ከዚህ ቀደም በተለያዩ የካፍ መድረኮች የሰራዋቸው ስራዎች ለዚህ ሹመት ትልቅ እገዛ አድርገውልኛል። በዚያን ወቅት በትጋት እና በጥንካሬ ሰርቻለው ፤ ከዚህ በኋላም ሁሌም ለመሻሻል እና ይበልጥ ለመስራት እጥራለው።”

ሹመቱ ለሌሎች ስላለው ትርጉም…

“ሹመቱ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ይበልጥ እንዲሰሩ የሚያበረታታ ነው። ለኔም ይህ አጋጣሚ ያለኝን ክህሎት ለማሳየት እንዲሁም ሴቶች እግርኳስን ማስተዳደር እና ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ ለማሳየት ትልቅ ዕድል ይፈጥርልኛል።”

ስለ ኃላፊነቷ…

 “እንደማስበው ካፍ ስለሴቶች የእግር ኳስ ልማት ሲያስብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እኔም የሴቶች እግርኳስ ልማት ክፍል ኃላፊ እንደመሆኔ ከሴቶች እግርኳስ ዋና ኃላፊ እና ከካፍ ቴክኒክ ዳይሪክተር ጋር በመሆን የአፍሪካን የሴቶች እግርኳስ ወደ ፊት የሚያራምዱ ስትራቴጂዎች እና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ መስራት ይጠበቅብኛል። ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም በሙሉ ልቤ ተቀብዬዋለው።” 

ነገ በካይሮ ግብፅ ካፍ በሚያደርገው ስብሰባ በይፋ ኃላፊነቷን እንደምትረከብ ይጠበቃል።