የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደርጋል

የኢትዮዽያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሱዳኑ አል ሒላል ኦቢዬድ ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም 10:00 ላይ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከተደረገላቸው 26 ተጫዋቾች መካከል 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ነበር የዛሬ ሳምንት ልምምዱን ማድረግ የጀመረው። ጥሪ ተደርጎላቸው በክለብ ጨዋታ ምክንያት ያልተገኙ 9 ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር ሳይቀላቀሉ በመቅረታቸው ሲቀነሱ በምትኩም ከሲዳማ ቡና ፈቱዲን ጀማል እና ሐብታሙ ገዛኸኝ ፣ ከድሬዳዋ ከተማ ፍሬው ጌታሁን እና ገናናው ረጋሳን በመጥራት በመጥራት ዝግጅቱን ሲቀጥል የባህር ዳር ከተማዎቹ ምንተስኖት አሎ እና ወንድሜነህ ደረጄ ሁለት ቀን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ ከሰሩ በኋላ ለክለባቸው ለመጫወት ሄደው ሳይመለሱ በዛው ቀርተዋል።

በቡድኑ ጋር ተያይዞ ያለው አዲስ ጉዳይ ትላንት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የመከላከል እና የማጥቃት ኃይላቸውን ለማጠናከር በማሰብ ተመስገን ካስትሮ (ተከላካይ ከኢትዮዽያ ቡና) ፣ ኢብራሂም ሁሴን (ተከላካይ ከኢትዮ ኤሌትሪክ) እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል (አጥቂ ከመቐለ 70 አንድርታ) ጥሪ አድርገው ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ዝግጅት ጀምረዋል። በኃይሉ ተሻገር እና ፍሬው ጌታሁን ደግሞ ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ ያላለቀ ጉዳይ በመኖሩ ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።

ከ23 ዓመት በታች ቡድኑ ከሶማልያ ጋር የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ በኅዳር ወር የሚጠብቀው ሲሆን ሶማልያን አልፎ ቀጣይ ሁለት የማጣርያ ተጋጣሚዎቹን በድምር ውጤት ከረታ ልክ የዛሬ ዓመት በኖቬምበር 2019 ግብፅ ላይ ለሚስተናገደው የአፍሪካ 23 ዓመት በታች ዋንጫ ማለፍ ይችላል።