ለቀድሞ ታላቅ አሰልጣኝ ሥዩም አባተ የመታሰብያ ውድድር ተዘጋጀ

አንጋፋው የእግርኳስ ሰው ጋሽ ሥዩም አባተን የሚዘክር በስድስት የአንደኛ ሊግ ቡድኖች መካከል የእግርኳስ ውድድር በአልማዝዬ ሜዳ ተዘጋጀ።

የቄራ አንበሳ የእግርኳስ ማኅበር ባሳለፍነው ወር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው ታላቅ አሰልጣኝ ጋሽ ሥዩም አባተን ለማስታወስ እና ስራውን ለመዘከር በማሰብ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የአንደኛ ሊግ ተሳታፊ ቡድኖች የሆኑት ኮልፌ ቀራንዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ናኖ ሁርቡ፣ ልደታ ክ/ከተማ እና ጋሽ ሥዩም በቴክኒክ ዳሬክተርነት ያገለገሉበት ቄራ አንበሳ ተሳታፊ የሚሆኑበት ውድድር ከነገ ኅዳር አንድ ጀምሮ ቄራ በሚገኘው አልማዝዬ ሜዳ የሚካሄድ ይሆናል።

ጠዋት 02:00 በመክፈቻ ጨዋታ በመሐመድ ኢብራሂም (ኪንግ) የሚመራ በሥዩም አባተ የሰለጠኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ቡድን ከ በጌታቸው ካሳ (ቡቡ) የሚመራ በቄራ አንበሳ አልማዝዬ ሜዳ ይጫወቱ የነበሩ የቀድሞ ስመጥር ተጫዋቾች የሚጫወቱ ይሆናል። በመቀጠልም 03:00 ቄራ አንበሳ ከ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ፣ 05:00 አ/አ ፖሊስ ከ ናኖ ሁርቡ ይጫወታሉ።

የእግርኳስ ባለውለታዎቿን በቋሚነት የመዘከር ልምድ በሌላት ኢትዮጵያ ክለቦች አልያም ግለሰቦች በግል ተነሳሽነት እና ጥረት ከመዘከር ባለፈ በዘላቂነት ስማቸው ለቀጣዩ ትውልድ ህያው ሆኖ በቋሚነት የሚታወስባቸው ውድድሮች የሚዘጋጅበት መንገድ ቢፈጠር መልዕክታችን ነው።