ቻምፒየንስ ሊግ| በዓምላክ ተሰማ በመራው የፍፃሜ ጨዋታ ኤስፔራንስ ዴ ቱኒዝ ቻምፒዮን ሆኗል

ኢትዮጵያዊው አርቢቴር በዓምላክ ተሰማ በብቃት በመራውና በአንድ የካሌደር ዓመት የውድድር ፎርማት ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄደው የ2018 የቶታል የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ኤስፔራንስ ዴ ቱኒዝ የግብፁ አል አህሊን በድምር ውጤት አሸንፎ ቻምፒዮን ሆኗል። ከሳምንት በፊት አሌክሳንደሪያ ላይ 3-1 የተረታው ኤስፔራንስ በሜዳው ከጨዋታ ብልጫ ጋር አህሊን 3-0 በመርታት በድምር ውጤት 4-3 ነው ዋንጫውን ማንሳት የቻለው፡፡

በደማቁ ኦሎምፒክ ደ ራዴስ ስታዲየም የዓለም እግርኳስ የበላይ አካል ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የወቅቱ የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ የታደሙበት ይህ ታላቅ ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማ እየተመሩ ነበር ቡድኖቹ ወደ ሜዳ የገቡት። የጨዋታው የመጀመርየው አርባ አምስት ብዙም ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ኤስፔራንሶች ጫና ፈጥረውና ጨዋታውን በፍጥነት ተቆጣጥረው ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ቢያደርጉም የአህሊ የመከላከል አደረጃጀትን ማስከፈት አስቸግሯቸው የነበረ በመሆኑ ለጎል የቀረበ ሙከራ ማየት አልቻልንም ነበር። በጨዋታው 24ኛው ደቂቃ የኤስፔራንሱ ኩሊባሊ እና የአህሊው ሱሌማኒ በፈጠሩት ከኳስ ውጭ ጉሽሚያ አልቢትሩ በዓምላክ በተረጋጋ ሁኔታ በፈገግታ ለሁለቱም የቢጫ የማስጠንቀቂያ ካርድ ሰጥተቸዋል። በሌላ አጋጣሚ 33ኛው ደቂቃ በአህላሊ የግብ ክልል ኤስፔራንሱ ያሲን ኬኔሲ ጥፋት ተሰርቶብኛል በማለት ያቀረበውን ቅሬታ ኢተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ የቫር እገዛን በመጠቀም ፍፁም ቅጣት ምት የሚያሰጥ ጥፋት አለመሆኑን ተረድተው ጨዋታውን በማዕዘን ምት አስቀጥለዋል።

በጠንካራ ፉክክር ሆኖም በጎል ሙከራ ያልታጀበው ጨዋታ የመጀመርያው አርባ አምስት ያለ ጎል ወደ እረፍት ወጡ ሲባል 45ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተቀበለውን ኬኔሲ በጥሩ መንገድ ያቀበለውን በግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ ሰዓድ ባጉሪ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሮ የኤስፔራንስን ተስፋ አለምልሞ እረፍት ሊወጡ ችለዋል።

ውጥረት በተሞላበት እና ከፍተኛ ትኩረት በሳበው የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በ54ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረ ጎል ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሰዒድ ባጉሪ በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የኤስፕራንሰ ዋንጫ የማንሳት እድልን አስፍቷል። ከዚህ በኋላ መከላከል መንገዳቻው ያላዋጣቸው አህሊዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የማጥቃት ኃይላቸውን ቢያሰፉም ምንም የጎል እድል ሳይፈጥሩ ኤስፔራንስ በመልሶ ማጥቃት 86ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ የነጠቀውን ኳስ ወደ ፊት ይዞ በመግፋት አኒስ ባዳሪ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኤስፕራስ 3-0 አሸንፎ በድምር ውጤት 4-3 በመርታት የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።

በዚሁሉ የጨዋታ ሂደት ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ከጨዋታው ክብደት አንፃር የጨዋታውን ሚዛን በመጠበቅ ፣ ተገቢ የሆኑ ውሳኔዎችን በመወሰን በአግባቡ ጨዋታውን በፈገግታ በመቆጣጠር ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ ከፊፋ ፕሬዝደንት ኢንፋንቲኖ ሜዳሊያውን ተረክቧል።


በ1919 የተመሰረተው የቱኒዙ ኃያል ክለብ ኤስፔራንስ ከ1994 እና 2011 ቀጥሎ ሶስተኛ የአፍሪካ ክብር ሲቀዳጅ በቀጣይ ዓመት ለሚያከብረው 100ኛ የምስረታ በዓሉም ልዩ ገጸ-በረከት ሆኖለታል። ኤስፔራስ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ የ2.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ሲያገኝ አፍሪካን ወክሎ በታህሳስ ወር በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ በዚህ ተሳትፎም ተጨማሪ እስከ አንድ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት የሚያገኝ ይሆናል፡፡