ኢትዮጵያውያን ዳኞች የኦሊምፒክ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታን ይመራሉ

በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወንዶች እግርኳስ የአፍሪካ ዞን ቅድመ ማጣርያ ከኅዳር አምስት ጀምሮ የመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናሉ። የኢትዮጽያ ከ23 ዓመት በታች ቡድኑ በዕለተ ረቡዕ ከሱማሊያ ጋር ሲጫወት በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን ዳኞች ሲሸልስ ላይ ሲሸልስ ከ ሱዳን የሚያደርጉትን ጨዋታ ይመራሉ።

ረቡዕ ኅዳር 5 በቪክቶርያው ዩኒቲ ስታድየም የሚደረገውን ይህን የሲሸልስ እና ሱዳን ጨዋታ በዳኝነት እንዲመሩ ካፍ አራት ኢትዮጵያውያን ዳኞችን መድቧል። በ2018 መጀመርያ ላይ የካፍ እና የፊፋ ኢንተርናሽናል ባጅ የተረከበው ቴዎድሮስ ምትኩ የጨዋታው ዋና ዳኛ ፣ በረዳት ዳኝነት ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሸዋንግዛው ተባበል እና ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለራጉኤል ወልዳይ እንዲሁም በአራተኛ ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለሥላሴ ተመድበዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የካፍ እና የፊፋ ዋና ዳኛ ሆኖ ከተመደበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ አራተኛ ዳኛ በመሆን ያገለገለ ሲሆን ይህ ጨዋታን ዋና ዳኝ ሆኖ ሲያጫውት የመጀመርያው ነው።

በዓለም አቀፍ መድረክ ጨዋታዎችን መምራት የሚችሉ በሴት እና በወንድ 22 ኢንተርናሽናል ዳኞች ያሏት ኢትዮጵያ ከለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከፍ ያሉ አህጉራዊ ጨዋታዎችን በብቃት በመዳኘት በካፍ እና በፊፋ መልካም ስምን እያተረፈች ትገኛለች።

በተያያዘ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚደረገውን የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጨዋታ ቱኒዚያዊያኑ ጉዊራት ሀይተም (ዋና)፣ ረምዚ ሔርች (ረዳት) እና ኸሊል ሀሰን (ረዳት) የሚመሩት ይሆናል።