የግል አስተያየት | ኦሊምፒክ ቡድናችን እንዴት ነበር ?

አስተያየት በዘርዓይ ኢያሱ

በአቋም መለኪያ ጨዋታ ከ23 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡደን የሱዳኑን አል ሂላል ኦቢዬድን 2-0 ማሸነፉ የቡድኑን ተነሳሽነት ከመጨመር በዘለለ አሰልጣኞቹም የተጨዋቾቻቸውን ወቅታዊ ብቃት እንዲያዩ ያስችላቸዋል፡፡ ኦሊምፒክ ቡድኑ የፊታችን ረቡዕ ከሶማሊያ ጋር ለ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ያለበት እንደመሆኑ ድሉ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞቹ እና ተጫዋቾቹ ላይ ይነበብ የነበረው ስሜት በጨዋታው ደስተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

በርግጥም ጥቅል ነገሩን ስንመለከት ጨዋታው የተሻለ የጎል ዕድል የፈጠርንበት እና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰድንበት በመሆኑ ጥሩ ነገር አይተናል፡፡ የተገኙት የግብ ዕደሎችን አለመጠቀም ደግሞ አሁንም በብሔራዊ ቡድኖቻችን በኩል ያልተፈታ ችግር መሆኑን ታዝበናል፡፡


ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ዮሴፍ ዮሀንስ

ጨዋታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የተጠቀመው ፎርሚሽን 4-2-3-1 ነው፡፡ ፎርሜሽኑ የመከላከልና የማጥቃት ሚዛንን ለመጠበቅ ተመራጭ ሲሆን በዚህ ረገድ የአማካይ ተከላካዮቹ ሚና ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታድየም የሱዳኑን አል ሂላል ኦቢዬድን ሲገጥም በአማካይ ተከላካይ ስፍራ ዮሴፍ ዮሃንስ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ናቸው የተጣመሩት፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች የጨዋታ ባህሪያቸው ተመሳሳይ ከመሆኑ ባሻገር ቡድኑ ኳስ እንዲቆጣጠር በማድረግ ውስጥ የነበራቸው ሚና አስደሳች ነው፡፡

የረጅምና የአጭር ኳስ ስርጭት፤ ከተከላካዮቹ ፊት ለፊት ያለውን ክፍት ቦታ በትክክለኛው ሰዓት በመገኘት መሸፈን እና ቡድኑ በኳስ ቁጥር ብልጫ እንዲወስድ በማደረግ ረገድ የሁለቱ ሚና እጅግ ይበል የሚያሰኝ ነበር፡፡ እንዲሁም የሁለቱ አጨዋወት የግራ መስመር ተከላካዮቹ ወደፊት ሄደው ማጥቃት ቢፈልጉ እንኳን እንዲጫወቱ የሚጋብዝ መሆኑ ሌላው በጎ ነገር ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ቡድኑ በስድስት ተጨዋቾች ማጥቃት የሚያችልበት እድል ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጥምረት ከሞላ ጎደል የተዋጣለት ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡

ነገር ግን በዚህ አንድ ነገር ታይቶኛል፡፡ ረጃጅም ኳሶችን የሚጫወት ቡድን በሚያጋጥመን ግዜ በረጅሙ የሚጣለው ኳስ ተከላካዮቹ ላይ ጫና ከመፍጠሩ በፊት መግጨት እንዲሁም የተጋጣሚ ቡድን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ በሚወስድብን ግዜ ቅብብሎሹን ማቋረጥ የሚችሉት ብርታታቸው (endurance) ከፍተኛ የሆኑ የአማካይ ተከላካዮች ናቸው፡፡

እንዲህ አይነቶቹ አማካዮች በጨዋታ ባህሪያቸው ከእነ ቴዎድሮስ የተለዩ በመሆናቸው አማራጩን ለማስፋት ከላይ የተቀመጡትን ቴክኒኮች ሊያሟሉ የሚችሉ ተጨዋቾች አሉን ወይ የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ከመስመር እየተነሱ የሚያጠቁት ሐብታሙ ገዛኸኝ እና ዳዊት ማሞ ኳስ በተቃራኒ ቁጥጥር ስር በምትሆንበት ግዜ ወዳ ኋላ በማፈግፈግ የመስመር ተከላካዮቹን ለመርዳት ያደረጉት ጥረት ስለ ታክቲኩ ያላቸው ግንዛቤ ጥሩ መሆኑን ያሳያል፡፡

ግን ደሞ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ገናናው ረጋሳ (ለብሔራዊ ቡድኑ ሲጫወት ይህ የመጀመሪያው ሰለሆነ ስህተት ለመቀነስ ይመስላል) ወደፊት ሄዶ ለመጫወት የነበረው ድፍረት ውስን ስለነበር ሐብታሙ ለማጥቃት ከሄደበት ለመመለስ ብዙ ርቀቶችን እንዲሮጥ አስገድዶታል፡፡ በመሆኑ የሀብታሙ የማጥቃት ሃይሉ ሲደክም ተመልክተናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቴዎድሮስ እና ዮሴፍ ለዳዊት ማሞ እና ለሀብታሙ ገዛኸኝ ደጋግመው ወደ መስመር ያወጧቸው የነበሩ ረጃጅም ኳሶች ተፅዕኖ ፈጣሪ ስለነበሩ በእኔ በኩል አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው፡፡

ቴዎድሮስ ታፈሰ እና የዓብስራ ተስፋዬ

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከመጀመሪያው ግማሽ መልስ የተጫዋች ለውጥ ሲያደርግ ሳይቀየሩ ሙሉ ጨዋታ ያጠናቀቁት ቴዎድሮስ ታፈሰና ፈቱዲን ጀማል ብቻ ናቸው፡፡ በለውጡ ምክንያት በአማካይ ተከላካይ ስፍራ እንዲጣመሩ የተደረጉት ቴዎድሮስ ታፈሰ እና የዓብስራ ተስፋዬ ሲሆኑ ምንም እንኳን ፎርሜሽኑ ተመሳሳይ ቢሆንም ትግበራው ግን የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የዓብስራ ተፎጥሮዊ የአማካይ ተከላካይ ባለመሆኑ ከቴዎድሮስ አጠገብ እንዲጫወት ቢደረግም ጨዋታው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በሚሄድበት ጊዜ የአብስራም በማጥቃት ውስጥ ከሚሳተፉ ተጨዋቾች ጋር ሲደባለቅ ተመልክተናል፡፡ ይህ በክለቡ ውስጥ የሚያደረገው ልማድ ሲሆን ያለው የቴክኒክ ብቃትም ይህን ለማድረግ ያስገድደዋል፡፡
በመሆኑም የእሱ እንቅስቃሴ የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-1-4-1 ፎርሜሽን በመቀየሩ የብሄራዊ ቡድኑ የማጥቃት ኃይል ከፍ እንዲል እገዛ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን አብስራ የመከላከል ሽግግር አነስተኛ በመሆኑ የቡደኑን የመከላከል ሚዛን የመጠቡቁ ኃላፊነት በቴዎድሮስ ታፈሰ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል፡፡ ይህ ማለት የአብስራ መጫወት አልነበረበትም ማለት ግን አይደለም፡፡

ቴዎድሮስ ኳስ በማሰራጨት የሚታወቅ እንጂ ነጣቂ አማካይ ባለመሆኑ ቢያንስ ከአጠገቡ ሳይርቅ የሚያግዘው ተጨዋች ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ስላልሆነ ሁለተኛው ግማሽ ከተጀመረ በኋላ በአል ሂላል ኦቢዬድን አማካዮች የመጣውን ጫና ለመጋፈጥ ተቸግሮ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ የአብስራ ሲገባ ለተከላካዮቹ በቂ የመከላከል ሽፋን የሚሰጥ፤ ኳስ ማስጣል የሚችል ተጨዋች ቢኖር እሱም ከአማካይ ተከላካዩ እየተቀበለ ጨዋታውን ወደ ፊት መውሰድ የሚችልበትን ዕድል ይፈጥርለታል፡፡ በነበረበት የሚቀጥል ከሆነ ግን የአማካይ ተከላካዩን አጨዋወት ከግምት በማስገባት የመስመር ተከላካዮቹም የማጥቃት ሞራል የሚያሳጣው በመሆኑ የቡድኑን የማጥቃት ኃይል ይቀንሰዋል፡፡

በ4-2-3-1 ግዜ ሁለቱ የአማካይ ተከላካዮች የቡድኑን ሚዛን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ የሚጣልባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የመስመር ተከላካዮቹ እንዲያጠቁ የሚሰጡት ዋስትና ለአንድ ቡድን ስኬት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ የአብስራ በቀኝ የአማካይ ተከላካይነት ቢሰለፉና የግራ መስመር ተከላካዩ ለማጥቃት ቢሄድ የመስመር ተከላካዩ ጥሎት የሚሄዳውን ክፍት ቦታ መሸፈን የሚኖርበት ይሆናል፡፡

ይሁን እንጂ የአብስራ በተፈጥሮው የአማካይ ተከላካይ ባለመሆኑ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት የነበረው ድርሻ አነስተኛ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሸዊት ዮሃንስ በጥልቀት ለማጥቃት እየሄደ ኳስ ወደ ተጋጣሚ ክልል ሲያሻማ ተመልክተናል፡፡ የአማካይ ተከላካዮች ድጋፍ በሌለበት ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የተጋጣሚ የመስመር ተጨዋቾች ወደ ኋላ ያፈገፍጉ ስለነበር እና የመከላከል ሽግግራቸው ደካማ ስለነበር ነው፡፡


የመስመር ተከላካዮች

በ4-2-3-1 የአንድን ቡድን የማጥቃት ኃይል ለማጠናከር የመስመር ተከላካዮቹ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እነሱ ቶሎ ቶሎ መሳተፍ ሲችሉ የቡድኑ የማጥቃት ኃይል የሚጨምር ሲሆን ሸዊት ዮሃንስ እና ሳሙኤል ዮሃንስ አልፎ አልፎ ወደ ፊት ገፍተው ለመሄድ የሞከሩት ነገር በጥሩ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

በዚህኛው ጨዋታ ቅኝት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የመስመር ተከላካዮቹ እንዴት እንዲጫወቱለት እንደፈለገ ባላውቅም ተጋጣሚው ቡድን በጥልቀት አፈግፍጎ እንደመጫወቱ የመስመር ተከላካዮቹ በሙሉ ልብ አጥቅተው መጫወት የሚችሉበት ዕድል ነበር፡፡ በርግጥ የመስመር ተከላካዮቹ ጥለውት የሚሄዱትን ቦታ ተጋጣሚው ቡድን በመልሶ ማጥቃት ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋት ይኖር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህን እንዳይሆን የአማካይ ተከላካዮቹ ተራ በተራ ወደ መስመር እየወጡ መንገዱን እየዘጉ እንዲከላከሉ ማድረግ ይቻላል፡፡


አጥቂዎቹ

በዚህ ክፍል ሁለት አይነት ነገር አይቻለሁ፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ ሃብታሙ ገዛኸኝ እና ዳዊት ማሞ በመስመር አጥቂነት፤ አቤል እንዳለ ከፊት አጥቂው እስራኤል እሸቱ ጀርባ ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡ በዚህ የጨዋታ ቅርፅ የመስመር አጥቂዎቹ ሃብታሙ ገዛኸኝ እና ዳዊት ማሞ በማጥቃትና በመከላከል ሂደት ውስጥ በመሳተፍ የመስመሩን የመጫወቻ ቦታ ሚዛን ለመጠበቅ ያረጉት ጥረት ስለ ቦታው ያላቸውን ግንዛቤ ያሳያል፡፡

አቤል እንዳለ ደግሞ ከሁለቱ አማካይ ተከላካዮች የሚሰጠውን ኳስ ወደ መስመር በማውጣትና ለፊት አጥቂው እስራኤል ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለማቀበል ያደረጋቸው እሳቤዎች በመጠኑም ቢሆን የተደራጀ ቡድን እንድናይ አስችሎናል፡፡ ከዚህ ውጪ የእስራኤል እሸቱን ልዩ ተግባር ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ (ቡድኑ ውስጥ ያየሁት ብቸኛው የ16፤50 አጥቂ) ነው፡፡ ይህ አጥቂ ሜዳ ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት ያሳየው እንቅስቃሴ አጥቂዎች ከማጥቃት ባሻገር ባሉበት ቦታ ሆነው እንዴት መከላከል እንዳለባቸው የተረዳ ተጨዋች ሆኖ አይቻለሁ፡፡

በተለይ ደግም የተጋጣሚ ተከላካዮች ጨዋታ መስርተው እንዳይወጡ ተጭኖ በመጫወት በኩል ስኬታማ ነበር፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ልንወስድ የምንችለው ሁለት ጊዜ ከተከላካዮቹ ቀምቶ ያልተጠቀመባቸውን አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ እስራኤል አጋጣሚዎችን አለመጠቀሙ በቀጣይነት ሊያሻሽለው የሚገባ ክፍተት ቢሆንም እሱ በአቅራቢያቸው እስካለ ድረስ የአል ሂላል ኦቢዬድን ተከላካዮች ኳስ መስርተው እንዳይጫወቱ ፈሪ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ሚናው ሜዳ ውስጥ እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ቡድኑን ጠቅሟል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

በሁለተኛው ግማሽ የተሰማሩት አጥቂዎች ከመጀመሪያው ግማሽ ጋር ሳወዳድረው በአስፈሪነት ይለያሉ፡፡ ቡልቻ ሹራ፤ በረከት ደስታ፤ አማኑኤል ገብረመስቀል እና አቡበከር ሳኒ በአንድነት ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡ ወደፊት ሲሄዱም ተካጣሚቸውን ማስጨነቅ ያውቁበታል፡፡ በእነሱ ቦታ በመጀመሪያው ግማሽ ከተጫወቱት ተጨዋች ጋር ሳወዳድራቸው ደመነፍሳቸው ወደ ማጥቃቱ የሚጎትታቸው እንጂ እንደ ሃብታሙ ገዛኸኝና እንደ ዳዊት ማሞ የማጥቃቱንና የመከላከሉን ሚዛን የሚጠብቁ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ባለው ሃይል ማጥቃት በሚያስፈልገው ጊዜ ማለትም የተጋጣሚን ተከላካዮች ተጭኖ መጫወት በሚፈልግበት ጊዜ የእነዚህ ተጨዋቾች መኖር በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን የምስማማበት ሐቅ ነው፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ጨዋታው ኦሎምፒክ ቡድኑ ጥሩ ስብስብ ያለው መሆኑን እና በአጭር ጊዜ ዝግጅት ምን መልክ እንዳለው የተመለከትንበት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ አማረጮች ሲካተቱበት የተዋጣለት ቡድን ሊኖረን እንደሚችል የሚያሳዩ ፍንጮችንም ያየንበት ነው፡፡
በተረፈ ግን ይህንን ፅሁፍ ስፅፍ የተጫወትነው ከትላላቅ ቡድኖች ጋር ቢሆን ኖሮ በሚል እሳቤ እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾችን በተመለከተ ክፍተታቸውን ለማንሳት ፍላጎት የነበረኝ ቢሆንም ዕድሜያቸውን እና ልምዳቸውን ከግምት በማስገባት ከጨዋታው በኋላ መንሳት መርጫለሁ፡፡

መልካም ዕድል!


*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡

*ለጸኃፊው ያለዎትን አስተያየት በዚህ ኢሜይል አድራሻ መላክ ይችላሉ | zeray.eyassu@gmail.com




ሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ ላይ አስተያየት መጻፍ ይፈልጋሉ?
ሶከር ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ያላችሁን አስተያየት አዘል ተቀብላ በድረ-ገጿ ላይ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ትገልጻለች፡፡
የምንቀበላቸው ጽሁፎች

-በኢትዮጵያ እግርኳስ እና ተያያዥነት ያላቸው ማናቸውንም ርዕሰ-ጉዳዮች

-ከ800 ቃላት ያላነሰ ወይም በላይ የሆነ

-በሌላ አካል ወይም ግለሰብ ከዚህ በፊት ተጽፎ ያልቀረበ

-ስነ-ጽሁፋዊ ይዘቱ ከፍ ያለ እና ለአንባቢያን ግልጽ የሆነ

-በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የተጻፈ

– ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ቢያተኩር ይመረጣል

-የግለሰብ ወይም ቡድን እምነት፣ ዘር፣ ሀሳብ እና አመለካከት፣ ሰብዓዊ ክብር የማያንቋሽሹ

አስተያየትዎን በፋይል አያይዘው (Attach አድርገው) በዚህ ኢሜይል አድራሻ ይላኩልን:- abgmariam21@gmail.com