በስታድየም የመግቢያ ትኬት ውይይት ተደረገ

በስታዲየም መግቢያ ትኬት ሽያጭ ዙርያ በሚያጋጥሙ ግድፈቶች የፌዴሬሽኑ ማርኬቲንግ ክፍል ፣ የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አመራሮች እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ውይይት አድርገዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኀበር በአዲስ አበባ ስቴዲየም በሚኖረኝ ጨዋታ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከትኬት ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ የጥቁር ገበያ ግድፈቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው መስተካከል ይገባቸዋል በማለት ለፌዴሬሽኑ ጥቆማ ማቅረቧል። ይህን ጥቆማ የተቀበለው ፌዴሬሽኑ ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚመለከታቸው አካላት ማለትም የፌዴሬሽኑ ማርኬት ክፍል ፣ ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ እና ጥቆማ አቅራቢው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ኃላፊዎች በተገኙበት ነበር በችግሩ ዙርያ ሰፊ ውይይት ያደረጉት ።

ጠቃሚ ሀሳቦች በተነሱበት በዚህ ውይይት ክለቡ ያቀረባቸው ጥቆማዎች ተገቢነት ያላቸው በመሆናቸው ከዚህ በኃላ መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኃላፊዎች በቀጣይ ማሽን ላይ ከሚቀመጡ ትኬት ቆራጮች አንስቶ በር ላይ የሚሰማሩ ተቆጣጣሪዎች ምደባ ድረስ ጥንቃቄ እና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ፤ ፌዴሬሽኑም ከዚህ በኋላ በቀረበው ጥቆማ መነሻነት ጠንከር ያለ ክትትል የማድረግ ስራ እንደሚሰራ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርም ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈፀሙ አብሮ እንዲሰራ በመነጋገር ውይይታቸውን አጠናቀዋል።