ካሜሩን 2019| ዋልያዎቹ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

የምድብ አምስተኛ ጨዋታቸውን እሁድ ኅዳር 9 በአዲስ አበባ ስታዲየም ከጋና ጋር የሚያደርጉት ዋልያዎቹ ዝግጅታቸውን አጠናክረው እየሰሩ ይገኛሉ።

በ2018 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ማጣሪያ ላይ ተካፋይ የሀኘችው ኢትዮጵያ ለእሁዱ ጨዋታ ከጥቅምት 27 ጀምሮ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን አራት ተጫዋቾች ሳያካትት 19 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

በዛሬ 10:00 ላይ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ በነበረው የብሔራዊ ቡድኑ ልምምድ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ (ከሲዳማ ቡና) ቡድኑን ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ተቀላቅሎ ልምምድ እየሰራ የሚገኝ አዲስ ተጫዋች ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙት (ሽመልስ በቀለ ፣ ዑመድ ኡኩሪ እና ጋቶች ፓኖም) ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በመቀላቀል ዛሬ የመጀመርያ ልምምዳቸውን ሰርተዋል። ቢኒያም በላይ ደግሞ ነገ አልያም ሐሙስ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።

ዋልያዎቹ አምበላቸው ጌታነህ ከበደን በጉዳት ለጋናው ጨዋታ የማይጠቀሙ መሆኑ መልካም የማይባል ዜና ሆኗል። ከጉዳት ጋር በተያያዘ ሌላ መረጃም የአፄዎቹ የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን ታፋው ላይ ባጋጠመው መጠነኛ ጉዳት ዛሬ ከቡድኑ ጋር ሳይቀላቀል ተነጥሎ የእርምጃ ልምምድ እየሰራ ቢገኝም ለጨዋታው ይደርሳል ተብሏል።

ጨዋታውን ለማድረግ የቀረው ጊዜ አነስተኛ በመሆኑ ቀለል ያሉ ኳስን መሠረት ያደረጉ በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተከፍለው ጨዋታ በማድረግ ልምዳቸውን ሰርተዋል። ዋልያዎቹ የደበዘዘ ተስፋቸውን ለማለምለም በመመሸነፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ እጅግ ወሳኝ ጨዋታቸውን እሁድ ኅዳር ዘጠኝ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።