አሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 4-0 ሶማሊያ

ዛሬ በ10፡00 በአዲስ አበባ ስታድየም ለ2020 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሶማሊያ አቻውን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 4-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞችም ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ከነበረን የአጭር ጊዜ ዝግጅት አንፃር ውጤቱ ከበቂ በላይ ነው ብዬ ነው የማስበው” አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ

የሶማሊያ ቡድን በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ኃይል የተቀላቀለበትን ጨዋታ የመረጠ ይመስል ነበር። የኛ ተጫዋቾች ደግሞ ኳስን ተቆጣጥረው ክፍተቶችን በመፈለግ ግብን ለማስቆጠር የነበረንን ዕቅድ አሳክተዋል። በአጠቃላይ ቡድኑ አዲስ እንደመሆኑ እና ብዙ ጨዋታዎችን ባለማድረጉ መጠነኛ የቅንጅት ችግሮች ሊኖሩበት ይችላሉ። ከነበረን የአጭር ጊዜ ዝግጅት አንፃር ግን ውጤቱ ከበቂ በላይ ነው ብዬ ነው የማስበው። የተጨዋቾቻችንን በራስ የመተማመን መንፈስም ከፍ የሚያደርግ ውጤት ነው። በቀጣይም ቡድኑ ለዋናው ቡድን መጋቢ ሆኖ ሌሎች ዕድሉን ያላገኙ ተጫዋቾችም ተካተውበት ተስፋ ያለው መሆኑን ያሳየን ጨዋታ ነበር።

” አብዛኞቹ ተጫዋቾቻችን ከሃያ ዓመት በታች ናቸው” አሰልጣኝ መሀመድ ፈርያህል

ስለጨዋታው…

ጨዋታው በኢትዮጵያ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህ እግር ኳስ ነው ፤ ምንም ቅሬታ የለኝም። ነገር ግን ሦስት ጉዳዮችን ማንሳት እፈልጋለው። የመጀመሪያው ስለተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ነው። ሌላው ትናንት ባደረግነው የቅድመ ጨዋታ ስብስባ ሙሉ የህክምና ዕራዳታ ከሁለት አምቡላንሶች ጋር እንደሚኖር ተነግሮን ነበር ፤ ሆኖም ያ አልሆነም። በመጨረሻም ኢትዮጵያዎችን በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው ቀጣዩ ጨዋታም መልካም ፉክክር የሚደረግበት እንዲሆን እመኛለው።

ስለቡድኖቹ የዕድሜ ሁኔታ…

አብዛኞቹ ተጫዋቾቻችን ከሃያ ዓመት በታች ናቸው። ከአምስት እና ስድስት ወር በፊት ለ17 ዓመት ቡድኑ የሚጫወቱም ነበሩ። ፍላጎቴም ልምድ እንዲያገኙ ነው። የተቆጠሩብን ጎሎች ከእግር ኳስ ዕውቀት ማነስ ሳይሆን ከልምድ ማጣት የመጡ ነበሩ። ተጫዋቾቼ አብዛኞቹ ከአካዳሚ የተገኙ ናቸው። ወደፊትም እንደምንሻሻል አስባለው። በኢትዮጵያም በኩል ተመሳሳይ ነገር ብጠብቅም ከሃያ ሦስት ዓመት በላይ የሆኑ ተጫዋቾችን ተመልክቻለው።