ከፍተኛ ሊግ | ጅማ አባቡና አመራሩን በአዲስ መልክ አዋቀረ

ከኢትዮጵያ እግርኳስ ለረጅም ጊዜ ከጠፋ በኋላ በ2004 በድጋሚ ተመስርቶ በ2009 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በማደግ የመጀመሪያው የደቡብ ምዕራብ ክለብ መሆን የቻለው ጅማ አባ ቡና ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ ከጫፍ ቢደርስም በመጨረሻ ጨዋታ በስሑል ሽረ ተሸንፎ ሳይሳካለት መቅረቱ የሚታወስ ነው።

ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ ጉዞ ቢያደርግም በአስተዳደራዊ እና በፋይናንስ ችግር ለተጫዋቾች ደምወዝ ለመክፈል እስከመቸገር ደርሶ እንደነበርና ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ለፌዴሬሽን አቤቱታ ሲያሰሙ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህም ምክንያት ክለቡ የፋይናንስ ችግር ውስጥ መግባቱን በመግለፅ የፋይናስ ድጋፍ እንዲደረግለት ጥሪ አስተላልፎም ነበር።

ከዚህ ሁሉ ውጣውረዶች በኃላም ክለቡ እንደክለብ የመቀጠል ህልውናው አጠያያቂ ደረጃ የደረሰ ቢመስልም በስተመጨረሻ ክለቡ የአሰልጣኞች ቅጥር በመፈፀም በዘንድሮው ከፍተኛ ሊግ ማዕከላዊ ደቡብ ምዕራብ ምድብ እንደሚሳተፍ ተረጋግጧል፡፡

ከክለቡ ህልውና በመቀጠል ይጠበቅ የነበረው የጠቅላላ ጉባዔ በዛሬው እለት ሲከናወን ያለፉትን ሦስት ዓመታት የኦዲት ሪፖርት በማፅደቅ በቀጣይ 12 አባላት ባሉት ቦርድ እንዲመራ ተወስኗል። ከነዚህም መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ሆራይዘን ፕላንቴሽን በቦርድ አባልነት በአዲሱ አወቃቀር ተካተዋል። የደጋፊ ማህበርም አንድ ተወካይ በቦርድ አባል ውስጥ በታዛቢነት እንዲገኝ በመወሰን የቀድሞዎቹን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በክብር ተሸኝተዋል።

በጠቅላላ ጉባዔው በተላለፈው ውሳኔ መሰረት አቶ ሰብስብ አባፊራ አዲሱ የጅማ አባ ቡና ፕሬዝዳነት ሆነው ሲመረጡ ቀጣይ የክለቡ አካሄድ ላይ የተደረጉ ለውጦችንም የክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ አስታውቀዋል። ” ከዚህ በኋላ ጅማ አባ ቡና በአካባቢያዊና በሀገር በቀል ተጫዋቾች ያተኩራል፤ ለውጭ ሀገር ተጫዋቾች ቦታ አይኖረውም፤ የተጫዋች ደሞዝ ከ25,000 ብር በላይ አይከፍልም፤ ዳግመኛ በፋይናንስ ችግር ውስጥ እንዳይባ የራሱን ገቢ በሚያስገባባቸው ስራዎች ላይ ትኩረት ተጥቶ ይሰራል።” ሲሉም ገልፀዋል።