ደደቢት ከፋይናንስ ችግሩ ፋታ አግኝቷል

ባለፉት ቀናት በፋይናንስ ችግር ምክንያት ህልውናው አስጊ ሁኔታ ላይ ደርሶ የነበረው ደደቢት በፕሪምየር ሊጉ እየተወዳደረ እንደሚቆይ ተረጋግጧል።

የአንድ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን ደደቢት በፋይናንሱ ረገድ እንደ ክለብ የነበረው ጥንካሬ አደጋ ውስጥ ገብቶ መሰንበቱ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ክለቡ በክረምቱ የዝውውር ፖሊሲውን በመቀየር እና መቀመጫውንም ወደ መቐለ ከተማ በማዞር ለመወዳደር ወስኖ ነበር። ሆኖም ችግሩን ለመቅረፍ ባለመቻሉ ከአጋር ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የሞከረበት መንገድ መሳካቱን ተከትሎ ህልውናው እንደሚቀጥል ታውቋል። ላለፉት ቀናት ለትግራይ ክልል መስተዳድር ጨምሮ ለበርካታ ድርጅቶች ደብዳቤ በማስገባት የተቋሞቹን ምላሽ ሲጠብቅ የነበረው ክለቡ ተሳክቶለት ከጠየቃቸው ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱ ሲታወቅ በቀጣይ ቀናትም የሌሎች ድርጅቶችን መልስ እየተጠበቀ እንደሆነ ከክለቡ ያገኘነው መረጀ ያመለክታል።

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በሜዳው የተጫወተው እና ምንም ነጥብ ማሳካት የተሳነው ደደቢት በቀጣይ ሳምንት በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳው ውጪ በሃዋሳ ከተማ ደቡብ ፖሊስን የሚገጥም ይሆናል።