ጋና 2018 | የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ሊዲያ ታፈሰ በዋና ዳኝነት በመራችው ጨዋታ ተጀመረ

የ2018 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ዛሬ ሲጀመር ሊዲያ ታፈሰ በመራችው የመክፈቻ ጨዋታ አስተናጋጇ ጋና አልጄርያን አሸንፋለች።
በምድብ ሀ የሚገኙት ጋና እና አልጄርያ ሴት ብሔራዊ ቡድኖች በአክራው ኦሄኔ ጃን ስታድየም ያደረጉትን ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በዋና ዳኝነት የመራችው ሲሆን ክዊንሲ ቪክቶሬ እና ሜሪ ንጆሮጌ በረዳት ዳኝነት አብረዋት አጫውተዋል። ጋና በግላዲያ አምፎቢ የ13ኛ ደቁቃ ጎል ጨዋታውን 1-0 ስታሸንፍ ሊዲያ ታፈሰም ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ መርታ ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶችንም መዛለች። 

በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድረሮች ላይ በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን እየመራች የምትገኘው ሊዲያ ታፈሰ በ2016 የካሜሩን የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታንም በዋና ዳኝነት መምራቷ የሚታወስ ነው። 

የአፍሪካ ዋንጫው ዛሬ ምሽት በሌላ የምድብ ሀ ጨዋታ ሲቀጥል 3:30 ላይ ማሊ ከ ካሜሩን ይጫወታሉ።