ከባለሜዳ ጋር መጫወት ቀላል አይደለም – የጋና አሰልጣኝ ክዌሲ አፒያህ

በ2019 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አምስተኛ የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያ 10:00 ላይ ጋናን ታሰተናግዳለች። በጨዋታው ዙርያ የጋናው አሰልጣኝ ክዌሲ አፒያህ የሰጡትን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ስለዝግጅታቸው

ከማክሰኞ ጀምረን ኬንያ ነበርን፤ በሚገባ ተዘጋጅተናል። ጨዋታ ነገ ሆኖ ዛሬ ላይ ከባድ ልምምድ አትሰራም ስለዚህም እንዳያችሁት ዛሬ ቀለል ያለ ልምምድ ነው፡፡

ስለከተማው አየር ሁኔታ 

ኬንያ ሄደን ለመዘጋጀት የመከርነው ለዛ ነው፤ በርግጥ የአዲስ አበባ ከባህር ጠለል በላይ ከኬንያም ከፍ ብላ ነው የምትገኘው። አየሩ ብዙ እክል አይሆንብንም፡፡ ዓላማችን  እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ ነው፡፡ ዝግጅታችን ለማሸነፍ ነው ለዛም ነው ልጆቹን ዛሬ ያመጣዋቸው፡፡ ከባለሜዳ ጋር መጫወት ቀላል አይደለም፣ ሜዳውን በሚገባ ያውቁታል ደጋፊ አለ ስለዚ ቀላል አይደለም፡፡

ከኬንያው ጨዋታ በኋላ ስለተጠሩ አዳዲስ ተጫዋቾች

ይሄ ቡድን አዲስ ቡድን አይደለም፡፡ ለአስር ዓመታት አብሮ የሰራ ቡድን ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች ምን መስራት እንደሚችል በሚገባ አውቃለው፡፡ ከያንዳንዱ ጨዋታ በፊት የቱን ቡድን ለምን ዓይነት ጨዋታ ይዤ እንደምሄድ አውቃለው፡፡ ጋና እጅግ ብዙ ልጆች አሏት ከጨዋታው በፊት ይሄን ወይም ያን ልጅ፣ ወይም ቡድን ይሻለኛል የሚል ውሳኔ ነው የምወስነው፡፡

ስለደጋፊ

የሚጫወተው ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ እኔም ኢትዮጵያዊ ብሆን ብሔራዊ ቡድኔን እደግፋለው፡፡ ኢትዮጵያዊ እስከሆንክ ድረስ የብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ምንም ይሁን ምን ቡድንህን ትደግፋለህ፡፡

አሁን ከምድቡ ሁለተኛ ላይ ያለችው ጋና ለአፍሪካ ዋንጫ ታልፋለች?

ጋና ያለምንም ጥርጥር ታልፋለች፡፡ እንዳልከው ያልተጫወትነው ሁለት ጨዋታ አለን ስድስት ነጥብ ካገኘን ሌላ ምን እንፈልጋለን፡፡

ስለፕሬዝዳንቱ በሜዳ ተገኝቶ ማበረታታት

እዚ እስከደረስንበት ሰዓት እሱ እዚ መሆኑን አላወቅንም ነበር፡፡ እዚ ስንደርስ እዚ መሆኑንና ሊያየንም እንደሚመጣ ተነገረን፡፡ አንተ የሃገር መሪ ሆነህ ሌላ ሃገር ስብሰባ ላይ እያለህ የሃገርህ ልጆች ደግሞ ሀገር ወክለው እዛው ሀገር እያሉ ባትመጣና ባታያቸው በፍጹም ልክ አይሆንም፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሞ መጥቶ አይቶናል። ይህም በፕሬዝዳንታችን እንድንኮራ ነው ያደረገን፡፡