ድህረ ጨዋታ አስተያየት| ኢትዮጵያ 0-2 ጋና

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አምስተኛ ጨዋታውን በሜዳው ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና አቻው የ2ለ0 ሽንፈትን አስተናግዷል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ክዊሴ አፒያ- ጋና

“ከመጫወቻው ሜዳ ሁኔታና ከአየር ሁኔታው አንጻር ተጫዋቾቼ የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ ጨዋታው ቀላል የሚባል አልነበረም ፤ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ተጫዋቾቼ ለመተንፈስ ሲቸገሩ አስተውያለሁ። የሆነው ሆኖ በዚህ የአየር ሁኔታ ተጫዋቾች ለዘጠና ደቂቃ ሲሮጡ በማየቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከታክቲክ አንጻር በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን እንደማስቆጠራችን በሁለተኛው አጋማሽ ለመተግበር ያሰብን የአየር ሁኔታውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር ነበር ከዚህ የተነሳ ተጋጣሚያችን ኳሱን በይበልጥ መቆጣጠር ችለዋል፤ ኳሱን በይበልጥ እነሱ በመያዛቸው ለእኛ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቶን የነበረውን የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ ለመቋቋም ጥሩ እድልን ፈጥሮልናል፡፡”


አብርሃም መብራቱ – ኢትዮጵያ 
ስለ ጨዋታው

“የጋና ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ስብስብ እንዲሁም ከፍተኛ ስም ያላቸው ተጫዋቾችን ያካተተ ቡድን ነው፡፡ በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው 20 ደቂቃዎች ከጥንቃቄ ጉድለት ከገቡብን ግቦች በስተቀር ቡድናችን በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ብልጫ ወስደን ለመጫወት ችለናል፡፡ ጨዋታው በአንድ በኩል ያለንን አቅም ያሰየን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከጨዋታው ጥሩ ልምዶችን ይዘን የወጣንበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

“በሁለተኛው አጋማሽ ያገኘናቸውን እድሎች መጠቀም ብንችል ኖሮ የጨዋታውን ውጤት መቀየር ያስችለን ነበር፡፡

“በመጀሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ተጫዋቾቼ ካሳዩት መዘናጋት በስተቀር በቀሩት ደቂቃዎች ያደረግነው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡”

ስለ ብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ

“ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ቡድን መገንባት ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ይህ ቡድን ገና መገንባት ከጀመረ አጭር ጊዜ ነው ያስቆጠረው። ስለዚህ እስካሁን ባየናቸው ጨዋታዎች በየቦታው የተሻለ እንቅስቃሴ ላሳዮ ልጆች እድል እየሰጠን እንገኛለን ወደፊት ደግሞ ሊጉን በሚገባ መከታተል ስንጀምር ከዚህ በተሻለ ጠንካራ ቡድን ይኖረናል፡፡ ስለዚህ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን የመለየት ስራ ገና በሂደት ላይ ያለ ነው፡፡”

ስለ ጠንካራው የቡድኑ ክፍል

“እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ውስጥ የአማካይ ክፍሉና የአጥቂው ክፍል የተሻሉ ነበሩ ብሎ መናገር ይቻላል ነገርግን አሁንም የተከላካይ ክፍላችን ላይ ክፍተቶች ቢስተዋሉም፤ አሁንም ቢሆን ግን የምናገኛቸውን የግብ እድሎችን ወደ ግብ መቀየር ላይ መስራት ይኑርብናል፡፡”


በዛሬው ጨዋታ ሀገሩን በአምበልነት እየመራ የገባው አንድሬ አዬው ይህን ብሏል:-
ስለ መጫወቻ ሜዳው

“በቅድሚያም ወደዚህ ስንመጣ ሜዳው አስቸጋሪ እንደሚሆን እናውቅ ነበር በዚህም የተነሳ አሰልጣኛችን በመጀመሪያ 30ደቂቃዎች ግቦችን እንድናስቆጥር ይፈልግ ነበር እስሱን ለማሳካት የተቻለንን ጥረት አድርገናል፡፡እንደ አጠቃላይ ቡድናችን ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ስለሆነ በአጠቃላይ የጨዋታ እንቅስቃሴያችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡”

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

“ከሜዳ ውጪ የተደረገ ጨዋታ እንደመሆኑ በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኛችን ባዘዘን መሠረት ኳሱን እንዲይዙ ፈቅደን የአማካይ እና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን ጫና ውስጥ በመክተት የምናገኛቸውን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ሞክረናል፡፡”

error: Content is protected !!