ከፍተኛ ሊግ | ስልጤ ወራቤ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የበርካቶቹን ውል አድሷል

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ስልጤ ወራቤ ከአሰልጣኝ እስከ ተጫዋች በርካታ ለውጦችን በማድረግ አሁን ደግሞ አዳዲስ አስራ ሁለት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም አስራ ስድስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ደግሞ አራዝሟል፡፡

ስልጤ ወራቤ አስቀድሞ በምክትል አሰልጣኝነት ሲሰራ የቆየው አብዱልወኪል አብዱልፈታህን በዋና አሰልጣኝነት እንዲሁም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የእግርኳስ ተጫዋችነት ቆይታ በኋላ ጫማውን የሰቀለው ገረሱ ሸመናን በረዳት አሰልጣኝነት በመሾም ለዘንድሮው የውድድር ዓመት ዝግጅት የጀመረው ክለቡ የጀመረው ክለቡ አሁን ደግሞ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ ይገኛል። በክለቡ ውስጥ ውላቸው ተጠናቆ የነበሩ 16 ተጫዋቾችን ውል ካራዘመ በኋላም 12 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ አምጥቷል።

ወደ ክለቡ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው:-

በሽር ደሊል (ግብ ጠባቂ ከጅማ አባቡና)፣ አስቻለሁ ኡታ (አማካይ ከሀላባ ከተማ)፣ ሰዒድ ግርማ (አማካይ ከሀምበሪቾ)፣ መሀመድ ከድር (አማካይ ከሀድያ ሆሳዕና)፣ ተስፋዬ ሰለሞን (አማካይ ከሀድያ ሆሳዕና)፣ ኩሴ መጨራ (አጥቂ ከዲላ ከተማ)፣ ተመስገን ዱባ (አጥቂ ከወላይታ ድቻ)፣ ጎሳዬ ዳቢ (ተከላካይ ከሻሸመኔ ከተማ)፣ ፍሬው ኪዳኔ (ተከላካይ ከሀድያ ሆሳዕና)፣ ጢሞቴዎስ ቢረጋ (ተከላካይ ከደቡብ ፖሊስ)፣ ሐብታሙ መዝገቡ (ተከላካይ ከቡታጅራ ከተማ)፣ መሐመድ ናስር (አጥቂ ከሀላባ ከተማ) ሲሆኑ ክለቡ በቀጣይም ክፍተት ባለበት በተለይ በተከላካይ ክፍል ላይ ተጨማሪ ተጫዋች ለማምጣት ማቀዱን አሰልጣኝ አብዱልወኪል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ አዲስ ፎርማት በምድብ ሐ (ደቡብ ምዕራብ) የተደለደለው ስልጤ ወራቤ በደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ አቋሙን የፈተሸ ሲሆን ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ከገባም ሶስት ሳምንታት አልፈውታል፡፡