የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን በተሳታፊ ቁጥር ቀንሶ ተጀምሯል

የ2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ከአምናው በተሳታፊ ቁጥር ቀንሶ ከእሁድ እስከ ረቡዕ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ተጀምሯል።

በ2010 በተዋቀረው አዲሱ ፎርማት መሠረት በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከ5ኛ ደረጃ በታች ባጠናቀቁ እና አዲስ በተቋቋሙ በድምሩ 14 ክለቦችን ይዞ የተጀመረው ሁለተኛ ዲቪዝዮኑ በሀገሪቱ ከተደረጉ ሌሎች የሊግ ውድድሮች በተሻለ በታቀደለት ጊዜ ተከናውኖ ጥረት ኮርፖሬት፣ አርባምንጭ ከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን አሳድጓል።

አምና ከነበረው መነቃቃት አንጻር ዘንድሮ የተሳታፊዎች ቁጥር ይጨምራል አልያም ባለበት ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም የውድድር ዓመቱን የጀመሩት ስምንት ቡድኖች ብቻ ናቸው። ከአንደኛ ዲቪዝዮን የወረዱት ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና በዚህ ሊግ ከማይወዳደሩት ውስጥ ናቸው። ሲዳማ ቡና የሴት ቡድኑን ሲያፈርስ ኤሌክትሪክ ደግሞ በአንደኛ ዲቪዝዮኑ ደደቢት የሴት ቡድን መፍረስ ምክንያት በነበረበት መቆየት ችሏል። በዚህም ምክንያት አዲስ ተመዝጋቢው መቐለ 70 እንደርታን ጨምሮ 13 ሊሆን ይገባው የነበረው የተሳታፊ ቁጥር ወደ 11 ወረደ። የውድድሩ የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት በተካሄደበት ወቅትም ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ እንደማይሳተፍ በመገለፁ ቁጥሩ ወደ 10 ቀነሰ።

10 ተሳታፊዎችን በመያዝ የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓቱ የተካሄደለት ይህ ውድድር በወጣለት መርሐ ግብር መሠረት ኅዳር 9 ቢጀመርም ሁለት ቡድኖች እንደማይሳተፉ በመገለፁ ቁጥሩ ወደ ስምንት ለመውረድ ተገዷል። ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ሴቶች ከፍተኛ ዲቪዝዮን እንደሚሳተፍ ሲገለፅ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚም ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ የተገለፀ ክለብ ሆኗል። በዚህም የመክፈቻ ጨዋታው እሁድ ኅዳር 9 ሻሸመኔ ላይ ተደርጎ ሻሸመኔ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማን 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

ሰኞ በአዲስ አበባ ስታድየም በቀጠለው ውድድር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ከ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በቂርቆስ 4-1 የበላይነት ተጠናቋል። ንፋስ ስልክ ላፍቶዎች በተሻለ እንቅስቃሴ ጨዋታውን ቢጀምሩም ቂርቆሶች ቀስ በቀስ የበላይነት በመውሰድ የበላይ መሆን ችለዋል። በሬዱ በቀ ለበ19 እና በ28 ኛው ደቂቃ ከርቀት አክርራ በመምታት ባስቆጠረቻቸው ጎሎችም የመጀመርያውን አጋማሽ 2-0 በመምራት አጠናቀዋል። ከዕረፍት መልስ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ንፋስ ስልኮች በ48ኛው ደቂቃ ማራችኝ አየለኝ ባስቆጠረችው ግብ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችሉም በ57ኛው ደቂቃ ትሁን ወሎ የቂርቆስን መሪነት በድጋሚ አስፍታለች። በ75ኛው ደቂቃ ደግሞ ጋብሪኤላ አበበ ተጨማሪ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በቂርቆስ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሰፊ ጎሎች እየተሸነፈ በሊጉ ግርጌ የሚያጠናቅቀው ንፋስ ስልክ ዘንድሮም በሰፊ ልዩነት በመሸነፍ ውድድሩን ጀምሯል።

በውድድሩ እንደሚሳተፍ በመጠበቁ በእጣ ድልድል ውስጥ ተካቶ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ ጋር 11:00 ላይ ሊያደርገው የነበረው ጨዋታም እንደማይሳተፍ በመታወቁ ፋሲል ከነማም ወደ አዲስ አበባ ሳይመጣ ጨዋታውም ሳይካሄድ ቀርቷል።

የሳምንቱ የመጨረሻ የጨዋታ ቀን ረቡዕ ሲካሄድ በ9:00 አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከአዲስ መጪው መቐለ 70 እንደርታ ባደረጉት ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲ በ15ኛው ደቂቃ ሀና ተስፋዬ በቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ 1-0 አሸንፈዋል። በ11:00 ሊካሄድ የነበረው የነበረው የቦሌ ክፍለ ከተማ እና የኢትዮጵያ ወጠቶች ስፖርት አካዳሚ ጨዋታ ደግሞ አካዳሚ የማይወዳደር በመሆኑ ሳይከናወን ቀርቷል።

የሁለተኛ ዲቪዝዮኑ ውድድር በቀጣይ ሳምንት በሚደረጉ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይቀጥላል:-