ሲዳማ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ | ቅድመ ዳሰሳ

ገና ከጅምሩ በተለያዩ ምክንያቶች በተበታተነ መልኩ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕረምየር ሊግ 18 ቀናት “እረፍት” በኋላ ነገ በሚደረግ የ3ኛ ሳምንት ጨዋታ ይቀጥላል። ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ 09;00 ሀዋሳ ከተማ ስታድየም ላይ የሚያደርጉት ጨዋታም የነገ ብቸኛው መርሐ ግብር ነው። 

የደቡብ ካስቴል ዋንጫ አሸናፊ በመሆን እና የሜዳው ጨዋታዎችን የሚያደርግበትን ከተማ ወደ ሀዋሳ በመቀየር የውድድር ዓመቱን የጀመረው ሲዳማ ቡና በመጀመርያው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማን በጸጋዬ ባልቻ እና አዲስ ግደይ ጎሎች 2-1 ማሸነፍ ችሏል። በሁለተኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ለመጫወት መርሐ ግብር ቢወጣለትም ወደ ሌላ ጊዜ በመሸጋገሩ ሳይከናወን ቀርቷል። ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለፍፃሜ ከመድረሱ ባሻገር የመጀመርያ ዓመት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን ከሪከርድ የሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከሜዳው ውጪ አድርጎ በወሰኑ ዓሊ ብቸኛ ጎል የ1-0 ድል በማስመዝገብ ታሪካዊ አጀማመር አድርጓል። በቀጣይ ከስሑል ሽረ ጋር በሜዳው ጨዋታ ለማድረግ መርሐ ግብር ቢያዝም እንደ ሌሎች በርካታ ጨዋታዎች ሁሉ ወደ ሌላ ጊዜ የመሸጋገር እጣ ደርሶታል። 

በጨዋታ አቀራረብ ደረጃ ሁለቱ ቡድኖች ተቀራራቢ የሆነ ስልትን ይከተላሉ። የመስመር አጥቂዎች ፍጥነት እና የአጨራረስ ብቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን ዋንኛ ግብ አስቆጣሪዎቻቸውም ከመስመር የሚነሱ ተጫዋቾች ኒቸው። በነገው ጨዋታም ሁለቱ መስመሮች ስራ በዝቶባቸው እንደሚውሉ ሲጠበቅ በአንድ ለአንድ ፍልሚያ የተሻለ የሚሆነው ቡድን ውጤት ይዞ የመውጣት እድል ይኖረዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል በልምምድ ወቅት ጉዳት ያስተናገደው አበባየሁ ዮሀንስ የመግባት እና ያለመግባቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን በኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ ተጎድቶ ከሜዳ የወጣው አማካዩ ወንድሜነህ ዓይናለም የሚመለስ ይሆናል። 

ባህር ዳር ከተማ በርካታ ተጫዋቾችን በነገው ጨዋታ ላይ ያጣል። ማራኪ ወርቁ ከጉዳት ባለማገገሙ የማይሰለፍ ሲሆን አጥቂው እንዳለ ደባልቄም ቡድኑ ዛሬ የመጨረሻ ልምምድ ሲሰራ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ የማይደርስ ይሆናል። አዲስ ፈራሚዎቹ ቶጎዊው አጥቂ ጃኮ አራፋት እና ጋናዊው ተከላካይ አሌክስ አሙዙ ደግሞ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ሁሉ የወረቀት ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው እንዲሁም ከቡድኑ ጋር በቂ ልምምድ ባለመስራታቸው አይጫወቱም። ዳግማዊ ሰለሞን በአንፃሩ  አምና በከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ የተላለፈበትን  ቅጣት ባለመጨረሱ ከቡድኑ ስብስብ ውጭ የሆነ ተጫዋች ነው። 


ዳኛ
 

ይህን ጨዋታ እንዲመራ የተመደበው ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ነው። ተፈሪ የነገው ጨዋታ በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ በመሐል ዳኝነት የሚመራው ጨዋታ ነው።


እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሲገናኙ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። 

– ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታውን በሜዳው ሲያደርግ ባህር ዳር ከተማ በተቃራኒው ሁለተኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታውን ያከናውናል። 


ግምታዊ አሰላለፍ 


ሲዳማ ቡና (4 3 3)

መሳይ አያኖ 

ዮናታን ፍሰሀ – ግርማ በቀለ – ሰንደይ ሙቱክ – ፈቱዲን ጀማል 

ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሀንስ – ወንድሜነህ ዓይናለም

ሐብታሙ ገዛኸኝ – ፀጋዬ ባልቻ – አዲስ ግደይ 

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ሣላምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጀ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ 

ኤልያስ አህመድ –  ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ዳንኤል ኃይሉ 

ግርማ ዲሳሳ – ፍቃዱ ወርቁ – ወሰኑ ዓሊ