ቻምፒየንስ ሊግ | ጅማ አባ ጅፋር ነገ ወደ ጅቡቲ ያቀናል

በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 የውድድር ዓመት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፈው ጅማ አባ ጅፋር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ነገ ወደ ጅቡቲ ይጓዛል።

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን በመሆኑ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያን የሚወክለው ጅማ አባ ጅፋር ከጅቡቲው ቴሌኮም ጋር በቅድመ ማጣርያው መደልደሉ ይታወቃል። የመጀመረያ ጨዋታውንም ማክሰኞ ጅቡቲ ላይ ለማከናወን በአሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደ ጊዮርጊስ እየተመራ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ነገ አመሻሽ ላይ ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል።

18 ተጫዋቾችን በመያዝ ሐሙስ ረፋድ ከጅማ ከተማ ተነስቶ አዲስ አበባ የገባው ቡድኑ መስቀል ፍላወር በሚገኘው 35 ሜዳ ላይ ልምምዱን እየሰራ ሲገኝ የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ የተመረጠው ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄ በደረሰበት መጠነኛ ጉዳት ሁለቱን ቀናት ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ አብሮ ያልሰራ ቢሆንም ነገ ወደ ጅቡቲ ከሚያቀናው ስብስብ ውስጥ ተካቶ እንደሚሄድ ሲታወቅ የተቀሩት ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።

ወደ ጅቡቲ የሚያቀኑት 18 ተጫዋቾች ስም ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች፡ ዳንኤል አጄይ፣ ዘሪሁን ታደለ

ተከላካዮች፡ አዳማ ሲሶኮ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ተስፍዬ መላኩ ፣ ያሬድ ዘውድነህ ፣ ከድር ኸይረዲ፣ ዐወት ገ/ሚካኤል ፣ መላኩ ወልዴ

አማካዮች፡ ንጋቱ ገ/ሥላሴ ፣ መስዑድ መሐመድ ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ ይሁን እንደሻው ፣ ኄኖክ ገምቴሳ ኤርሚያስ ኃይሉ ፣ አስቻለው ግርማ

አጥቂዎች: ዲዲዬ ለብሪ ፣ ሴዲቤ ማማዱ

የመጀመርያው ጨዋታ ማክሰኞ ጅቡቲ ላይ ሲከናወን የመልሱ ጨዋታ ደግሞ በሳምንቱ ማክሰኞ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚከናወን ይሆናል፡፡ አባ ጅፋር ይህንን ጨዋታ በድል ከተወጣ በመጀመርያው ዙር የ2018 የቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚው አል-አህሊን የሚገጥም ይሆናል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ስለ ቡድኑ ዝግጅት እንዲሁም አሰልጣኙ እና ተጫዋቾቹ የሰጡትን አስተያየት አመሻሹ ላይ ይዛ የምትቀርብ መሆኑን ከወዲሁ መጠቆም እንወዳለን።