ሊዲያ ታፈሰ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታን ትመራለች

በጋና አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ወሳን ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሲደረጉ አንደኛውን ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ አርቢቴር ሊዲያ ታፈሰ በዳኝነት ትመራዋለች፡፡

ካሜሩን ከናይጄርያ በ12፡30 አክራ ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ከዛሬ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብሮች አንደኛው ሲሆን ይህንን ጨዋታ ሊዲያ ታፈሰ በመሐል ዳኝነት ስትመራው ኬንያዊቷ ሜሪ ንጆርጌ እና ሞሪሸሳዊቷ ክዊንሲ ቪክቶርያ በረዳትነት አብረዋት የሚሩ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል ደግሞ ኬፕ ኮስት ላይ ደቡብ አፍሪካ እና ማሊ ሌላኛውን የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ያከናውናሉ፡፡

ሊዲያ ታፈሰ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ በጋና እና አልጄርያ መካከል ሲደረግ ዛሬ አብረዋት ከሚዳኙት ረዳቶች ጋር በዋና ዳኝነት መምራቷ የሚታወስ ሲሆን የዛሬው ጨዋታም በዚህ ውድድር ሁለተኛዋ ነው፡፡