“ዳኛው ሊረዳቸው እንዳሰበ በእኛ ላይ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ማሳያ ነበሩ “አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

በ2018/19 የካፍ ቶታል ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ትላንት ናይጄሪያ ላይ ሬንጀርስ ኢንተርናሽናልን የገጠመው መከላከያ 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። አሰልጣኝ ሥዩም ከበደም በጨዋታው ዙርያ ጠቅለል ያለ አስተያየት ሰጥተውናል። 

በጨዋታው ላይ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን ቢታይም የኒጀር ዜግነት ያለው የዕለቱ ዋና ዳኛ መሀመድ አሊ ሙሳ ባሳደሩት ጫና እንደተሸነፉ አሰልጣኝ ሥዩም ገልፀዋል። “የመጀመሪያው አጋማሽን በነፃነት እያጫወትን ነበር፤ ሁለታችንም እጅግ ጥሩ ነበርን። ግብ ሳይቆጠርም እረፍት ወጥተናል። ከእረፍት በኃላ ግን በጣም ጫናዎች በዙብን፤ በተለይ በተደጋጋሚ የቅጣት ምቶችና የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ይሰጥብን ነበር። በተቃራኒው እነሱ በሚያደርጉት ነገር ግን ውሳኔ አይሰጥም ነበር። እኔ ምክንያት የምፈልግ አሰልጣኝ ባልሆንም የተደረገብን ጫና በጣም ያሳዝናል። ሊረዳቸው እንዳሰበም የሚወስናቸው ውሳኔዎች ማሳያዎች ነበሩ። የእውነት ለተጋጣሚያችን እጅጉን ክብር አለኝ፤ ጥሩም ሲጫወቱም ነበር። እኛም ብዙ አጋጣሚዎችን አግኝተን መጠቀም አልቻልንም። የመጀመሪያው ጎል ሲቆጠርብን ተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬ ምንም ተጫዋቹ ላይ ጥፋት ሳይፈፅም ፍፁም ቅጣት ምት ሰጠብን፤ ያ ገባብን። ሁለተኛውም ጎል ሲገባብን በተመሳሳይ አጥቂያቸው ወደ ሳጥን ኳስ እየነዳ ሲገባ ማንም ጥፋት ሳይፈፀምበት ወደቀ፤ አሁንም ፍፁም ቅጣት ምት ሰጠብን። በተጨማሪም ለነሱ አንድም ካርድ ሳይሰጥ ለኛ አምስት መዞብናል።” 

አሰልጣኝ ስዩም ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየትም ከዳኝነቱ ጋር በተያያዘ ምን እንደተናገሩ በዚህ መልኩ ገልጸዋል። ” ይህ ዳኛ አይደለም። የሀገሬ ዳኞች በተከታታይ በብቃት እና በብስለት የአፍሪካን ውድድር እየመሩ ነው። በቅርቡ የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜን የመራው ኢትዮጵያዊ ነው። እነዚህ ዳኞች ካሉበት ሀገር መጥቼ ፍፁም ፍርሀት ያለበት ዳኛን ማየቴ የሀገሬ ዳኞች በሁሉም ነገር የተሻሉ እንደሆኑ እንደተረዳሁ ለሁሉም የናይጄሪያ ሚዲያ ገልጫለው። ይህን ጨዋታ እነዚሁ ሚዲያዎች የዳኛ እርዳታ የታከለበት በሚል በአርእስትነት እያወጡ እና የመልሱ ጨዋታም እንደሚከብዳቸው እየገለፁ ነው። ” ብለዋል።

መከላከያ የመልሱን ጨዋታ በቀጣዩ ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲያደርግ ሩዋንዳዊው ዳኛ ሳሙኤል ዩኪንዳ በመሀል ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል።