የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አንደኛ ሳምንት ውሎ 

ትላንት የተጀመረው የኢትዮጽያ ከፍተኛ ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን ዛሬ በ13 ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል። አራት ጨዋታዋች በተስተካካይ ሊከናወኑ ሲራዘሙ ከዚህ ቀደም የሚታየውን ደካማ ባህል ለመቀየር እንዲያስችል የዳኞች ኮሚቴ ከተያዘው ሰዓት አርፍደው በሚጀምሩ ክለቦችም ሆነ ዳኞች ላይ ቅጣት እንደሚያሳልፍ በማሳወቁ የዛሬዎቹ አመዛኝ ጨዋታዎች በተያዘላቸው ሰዓት ተከናውነዋል። 

ምድብ ሀ (መካከለኛ)

በዳዊት ጸኃዬ

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አምና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የወረደው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከአክሱም ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ታፈሰ ተስፋዬ ባስቆጠራት ግብ የከፍተኛ ሊግ ጉዞቸውን በድል ጀምረዋል፡፡ ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አክሱሞች በተደጋጋሚ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ከግብ ክልሉ ወጣ ባለ አቋቋም ላይ በተደጋጋሚ እየተገኘ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በተወሰነ መልኩ አለመናበቦችን ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡

በ16ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከራሳቸው ሜዳ በጥሩ ሁኔታ መስርተው የወጡት ኳስ በማራኪ መልኩ ወደ አክሱም የግብ ክልል ከደረሰ በኃላ ሲያሻግሩት አጥቂው ኄኖክ መሀሪ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ኳሱ የሄደበት መንገድ ጥሩ የሚባል ነበር። በቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ኳሱን መቆጣጠር ቢችሉም ከሜዳ ውጪ እንደመጫወታቸው ወደ ራሳቸው ግብ አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩትን የአክሱም ከተማዎችን የመከላከል አደረጃጀትን ለመስበር ግን ተቸግረው ተስተውሏል፡፡ በነዚህ ደቂቃዎች ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ከሚደረጉ ሞከራዎች ባሻገር በ37ኛው ደቂቃ ላይ ከማእዘን የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የመሀል ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ በግንባሩ በመግጨት የሞከራትና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ሌላኛዋ የቡድኑ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ እምብዛም ከመጀመሪያው የተለየ አልነበረም። በአመዛኙ የጨዋታ ክፍል ጊዜ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ አክሱም የሜዳ አጋማሽ አድልቶ ነበር የጀመረው፡፡ ነገርግን በተለይ በ59ኛው እንዲሁም በ61ኛው ደቂቃ ላይ አክሱም ከተማዎች በልዑልሰገድ አስፋውና በአንበላቸው ሰላማዊ ገብረስላሴ አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ 67ኛው ደቂቃ ላይ ሳይጠበቅ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ የአክሱሙ ግብ ጠባቂ መዘናጋትን ተመልክቶ ከሳጥን ውጪ በመምታት አስቆጥሯል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን በኢትዮ ኤሌክትሪኮች የ1ለ0 የበላይነት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። 

በጨዋታው በቅርቡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውሰት ውል ያመራው ወጣቱ ዮሃንስ ዘገየ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡

በሌሎች የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ሌላው ከፕሪምየር ሊግ የወረደው ወልዲያ ከሜዳው ውጪ ድል በማድረግ ዓመቱን ጀምሯል። ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጋር በኒያላ ሜዳ ጨዋታውን ያደረገው ወልዲያ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠረ ጎል 1-0 አሸንፎ ወጥቷል። ሰበታ ላይ ሰበታ ከተማ በኢብራሂም ከድር የፍፁም ቅጣት ምት እና ናትናኤል ጋንቹላ ግቦች ወሎ ኮምቦልቻን 2-0 ሲያሸንፍ ቡራዩ ላይ ደሴ ከተማን ያስተናገደው ቡራዩ ከተማ 1-0 አሸንፏል። ገላን ከተማ ከ ለገጣፎ እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ ከ አውስኮድ ያለ ጎል የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው።

ምድብ ለ (መካከለኛ እና ደቡብ ምስራቅ)

በአምሀ ተስፋዬ 

በዚህ ምድብ ትላንት አንድ ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ተካሂዶ ድሬዳዋ ፖሊስ ከአዲስ አበባ ከተማ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያተይተዋል። አዲስ አበባ ከተማ በጊት ጋትኮች የ28ኛ ደቂቃ ጎል ቀዳሚ ቢሆንም ጨተታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩ ፈርዓን ሰዒድ ያስቆጠረው ጎል ለባለሜዳዎቹ አንድ ነጥብ አስገኝታለች።

ዛሬ በመድን ሜዳ ኢኮስኮ እና ሀምበሪቾ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ጨዋታው ምንም እንኳ ጎል ባይሰተናገድበትም ብርቱ ፉክክር ታይቶበታል። በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ሀምበሪቾዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱ ሲሆን በዘካርያስ ፍቅሬ እና መልካሙ ፉንድሬ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ከሽፎባቸዋል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት ኢኮስኮች በረጃጅም ኳሶች የግብ እድሎች ፈጥረዋል። በ28ኛው ደቂቃ በየኋላሸት ሰለሞን የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ሲያደርግ በ36ኛው ደቂቃ ኄኖክ አወቀ ከርቀት የመታው ኳስ የግቡ አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች። በ38ኛው ደቂቃ አቤኔዜር ኦቴ የሙከረውና በግብ ጠባቂው የዳነበት ኳስም የሚጠቀስ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የቀረቡት ኢኮስኮች የተወሰደባቸውን ብልጫ ማስመለስ ሲችሉ በተቃራኒው ሀምበሪቾዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን መርጠዋል። በ75ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ ኢኮስኮ የግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ዘካርያስ ፍቅሬ ወደ ግብነት ይለውጠዋል ተብሎ ሲጠበቅ የኢኮስኮ ግብ ጠባቂ ያዳነበት በዚህ አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

በሌሎች የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ወደ ነጌሌ አርሲ ያመራው ኢትዮጵያ መድን ዮናታን ብርሀነ ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፎ ሶስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል። ናሽናል ሴሜንትን ከሀላባ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ 1-1 ተጠኔቋል። ሀላባ በአብዱልዓዚዝ ዑመር ጎል ቀዳሚ ቢሆንም ኤርሚያስ ቴዎድሮስ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል። ዲላ ከተማ ከወላይታ ሶዶ ከተማ ያለ ጎል አቻ ሲለያዩ ወልቂጤ ከተማ ከ የካ ክፍለ ከተማ ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገረ መርሐ ግብር ነው። 

ምድብ ሐ (መካከለኛ እና ደቡብ ምዕራብ)

በዚህ ምድብ ተጠባቂ የነበረው ሀድያ ሆሳዕና ከስልጤ ወራቤ ያደረጉት ጨዋታ በሆሳዕና 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለሀድያ ሆሳዕና ዳግም በቀለ፣ ፀጋው ድማሙ እና ትዕግስቱ አበራ የድሎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል። ነጌሌ ላይ ነጌሌ ከተማ ከቡታጅራ ከተማ 1-1 ተለያይተዋል። በ38ኛው ደቂቃ ክንዴ አቡቹ ቡታጅራን ቀዳሚ ሲያደርግ በ72ኛ ደቂቃ ላይ ምናሉ ታደለ ነጌሌን አቻ አድርጓል። ነቀምት ከ ቤንች ማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ሻሸመኔ ከተማ ከ ካፋ ቡና፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከ ጅማ አባ ቡና እንዲሁም ሺንሺቾ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ጨዋታዎች ናቸው።