ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ከ ደቡብ ፖሊስ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ነገ ወልዋሎ ከ ደቡብ ፖሊስ መቐለ ላይ በሚያደርጉት አንድ ጨዋታ ይጀምራል።

ነገ 9 ሰዓት ላይ በትግራይ ስታድየም የሚካሄደው በዚህ ጨዋታ ወልዋሎ አዲስ መጪው ደቡብ ፖሊስን ያስተናግዳል። በውድድር ዓመቱ ነጥብም ሆነ ጎል ማስመዝገብ ያልቻለው ወልዋሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በክለቡ ዙርያ ተፈጥረው የነበሩትን ክፍተቶች ሙሉ በሙሉ ፈትቶ ወደዚህ ጨዋታ እንደመቅረቡ ከባለፉት ጨዋታዎች የተሻለ የማሸነፍ ተነሳሽነት ይዞ ለጨዋታ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው ደቡብ ፖሊስም ባለፈው ሳምንት የዓመቱን የመጀመርያ ድል በደደቢት ላይ በማስመዝገብ በማሸነፍ መንፈስ ላይ እንደመሆኑ ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን ይገመታል።

ከባለፈው ዓመት በተሻለ በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ የሚጫወት ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነ ማርያም ባለፉት ጨዋታዎች በቡድናቸው ውስጥ የታየውን የጎል ማግባት ችግሮች ቀርፈው መግባት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች በዋነኝነት ከመሃል ለመሃል በሚደሩጉ እንቅስቃሴዎች ጥቃት ለማድረግ የሚሞከረው ወልዋሎ በአጨዋወቱ ብዙ የጎል እድሎች መፍጠር ባለመቻሉ ወደ አምናው የመስመር ላይ እና አብዱራህማን ፉሴይኒ፣ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ወይም ኤፍሬም አሻሞ ላይ ያተኮረ አጨዋወት ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በዘላለም ሽፈራው እየተመራ ባለፈው ሳምንት ሙሉ ሶስት ነጥብ ያሳካው ደቡብ ፖሊስ በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳው ውጭ እንደመውጣቱ በሜዳ ውጭ ጨዋታ የሚኖረው የጨዋታ አቀራረብን ለመገመት ቢያዳግትም ከአሰልጣኙ ባህርይ አንጻር በጥብቅ መከላከል እና እንዳለፉት ጨዋታዎች በመስመር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት ሊከተል እንደሚችል ይገመታል። በተለይም ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ብሩክ ኤልያስ በቡድኑ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና ሊወጣ የሚችል ተጫዋች ነው። 

ባለሜዳው ወልዋሎ አራት ተጫዋቾችን በጉዳት የሚያጣ ይሆናል። ከመቐለ ጋር በነበረው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው አስራት መገርሳ ከጉዳት ቢመለስም ለጨዋታው ብቁ ባለመሆኑ አይሰለፍም። ከዚ ውጭ በሳምንቱ አጋማሽ ጉዳት ያስተናገዱት ዳንኤል አድሓኖም፣ ኤፍሬም ኃይለማርያም እና ዳዊት ፍቃዱ በጨዋታው ቡድናቸውን የማያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው።

በደቡብ ፖሊስ በኩል ዘግይቶ ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው አዳሙ መሐመድ በጨዋታው እንደማይሰለፍ ሲረጋገጥ ባለፈው ሳምንት በጉዳት ቡድኑን ያላገለገለው የመስመር ተከላካዩ ዘነበ ከድር ከጉዳት አገግሟል።

የእርሰ በርስ ግንኙነት 

የነገው ጨዋታ የቡድኖቹ በታሪክ የመጀመርያ ግንኙነት ይሆናል። ደቡብ ፖሊስም በ2002 ትራንስ ኢትዮጵያን ከገጠመ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ መቐለ ያመራል።

ዳኛ

በዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታውን የሚመራው ፌዴራል አርቢቴር አዳነ ወርቁ ለጨዋታው የተመደበ ዳኛ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬታ

እንየው ካሳሁን – ደስታ ደሙ – በረከት ተሰማ – ብርሃኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – ብርሃኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሬችሞንድ አዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ 

ደቡብ ፖሊስ (3-5-2)

ዳዊት አሰፋ

ዘሪሁን አንሸቦ – ሳምሶን ሙልጌታ – ደስታ ጊቻሞ 

ብሩክ ኤልያስ – ሙሉዓለም ረጋሳ – አዲስዓለም ደበበ – መስፍን ኪዳኔ – አበባው ቡታቆ

በረከት ይስሃቅ – በኃይሉ ወገኔ