የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የድሬደዋ ከተማ ግብ ጠባቂ ለቀድሞ ክለቡ የትጥቅ ድጋፍ አደረገ

በርካታ ተጫዋቾችን በተለይ በድሬዳዋ ከተማ እና አካባቢዋ ማውጣት የቻለው ድሬዳዋ ፖሊስ ስፖርት ክለብ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂ ከሆነው ሳምሶን አሰፋ የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎለታል።

ሳምሶን ለቀድሞ ክለቡ ግምቱ 32 ሺህ ብር የሚያወጣ ሙሉ ትጥቅ ያበረከተ ሲሆን በርክክቡ ላይ በቀጣይ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለፅ ለዕለቱ የክብር እንግዳ ድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮምሽን እና የክለቡ የበላይ ሰብሳቢ ኮሚሽነር ጌታቸው አስረስ አስረክቧል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ለቀድሞ ክለባቸው የትጥቅ ድጋፍ ሲያደርጉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ሽመልስ በቀለ፣ ዑመድ ኡኩሪ እና ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና አብዱልከሪም መሐመድም በቅርብ ጊዜያት ይህን ተግባር ከፈፀሙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።