የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት – የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ትላንት በተደረገ አንድ ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ በዛሬው ዕለት አምስት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን እንዲህ ቃኝተናቸዋል፡፡


ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የደጋፊዎቻቸው የስታዲየም ድምቀት ሆነው መታየታቸው ነው። በጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም በ9 ሰዓት የሚገናኙበት ጨዋታም ከደጋፊ ድባቡ ባሻገር በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም የዚህ ሳምንት ተጠባቂው መርሐ ግብር ነው።

ከተጫዋች እስከ አሰልጣኝ በርካታ ለውጥን ያደረገው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ፋሲል ከነማ እስካሁን በሊጉ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጓል። ወደ ሀዋሳ አምርቶ በሲዳማ ቡና በሊጉ ጅማሮ ሽንፈትን ሲያስተናግድ በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ በታጀበው ጨዋታ ደግሞ በሁለተኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በመርታት የዓመቱን ሙሉ ሶስት ነጥብ አሳክቶ አንድ ጨዋታ ከመቐለ ጋር እየቀረው የአራተኛ ሳምንት ጨዋታውን ያደርጋል። የዲዲዬ ጎሜስ ኢትዮጵያ ቡናም እንደ ተጋጣሚው ሁሉ በርካታ የተጫዋቾች ለውጥን አድርጎ ዓመቱን ሲጀምር በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈ በኃላ ወደ መቐለ ተጉዞ ደደቢትን በማሸነፍ በድል መንገድ ላይ ሲገኝ ከወልዋሎ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የአራተኛ ሳምንት መርሀ ግብሩን የሚያደርግ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ተቀራራቢ የአጨዋወት መንገድን የሚከተሉ እንደመሆናቸው የአሸናፊነት ቅድመ ግምትን ለአንደኛው ቡድን ለመስጠት ከባድ ይመስላል። ፋሲሎች አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሀዋሳ ከተማ ቤት ከሚጠቀመው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን መሰረት ካደረገ አጨዋወት በመጠኑ ለወጥ በማድረግ ፈጣን ሽግግሮች እና ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ጥረት የሚያደርግ ቡድን በሁለቱ የሊግ ጨዋታዎች ላይ አሳይቶናል። ሆኖም የዛሬውን ጨዋታ በሜዳው እንደማድረጉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በዲዲዬ ጎሜስ አሰልጣኝነት መመራት ከጀመረ ወዲህ እንደየጨዋታው እና የሜዳ ባህርይ የሚለዋወጥ አጨዋወትን የሚከተል እንደመሆኑ በዛሬው ጨዋታ በታታሪ አማካዮቹ ተጠቅሞ የፋሲልን የመቀባበያ አማራጮች በመዝጋት ኳስ ሲያገኝ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚጥር ይጠበቃል።

ኢዙ ኢዙካ እና ሰለሞን ሐብቴን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ፋሲል ከነማ ፋሲል አስማማውን በጉዳት ያጣል። በቡና በኩል ዳንኤል ደምሱ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አህመድ ረሺድ ከብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት መልስ ቡድኑን የተቀላቀሉ ሲሆን ከቡድኑ ጋር ወደ ጎንደር የተጓዘው የአምበሉ አማኑኤል ዮሀንስ በጉዳት የመግባቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። ከወረቀት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ምክንያት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ያልቻለው ላይቤርያዊው አጥቂ ኩዊሀ ሾሌ ጉዳዩን ጨርሶ ለጨዋታ ዝግጁ መሆኑም ታውቋል፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

-ፋሲል ከነማ 2009 ሊጉን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል። ጎንደር ላይም ቡና አንድ ጊዜ ፋሲል አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።

– ባለፉት አራት ግንኙነታቸው 11 ጎሎች ሲቆጠሩ ፋሲል አራት፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሰባት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– ፋሲል ያለፉት ሶስት ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በፋሲል ከመሸነፉ ውጪ በአራቱ ማሸነፍ ችሏል።

ዳኛ

ኅዳር 18 የሊቢያው ኤል ናስር እና የደቡብ ሱዳኑ አል-ሒላል ጁባን ከኢትዮጵያዊያን ዳኞች ጋር ተመድቦ በአራተኛ ዳኝነት ያገለገለው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ከቻምፒየንስ ሊጉ መልስ ጨዋታውን እንዲመራ ተመድቧል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን

ያስር ሙገርዋ – ከድር ኩሊባሊ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ  – አብዱርሀማን ሙባረክ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታንቢ – ተካልኝ ደጀኔ

ሳምሶን ጥላሁን  – ዳንኤል ደምሴ – ካሉሻ አልሀሰን

አስራት ቱንጆ – ሎክዋ ሱሌይማን – አቡበከር ነስሩ


አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በውድድር ዓመቱ የአምናውን የአጀማመር ስኬታማነትን በሁለት ጨዋታዎች አብረውት እንደሌሉ የታየበት አዳማ ከተማ በጅማ አባጅፋር በሜዳው ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ ወደሚታወቅበት ተፎካካሪነት ለመመለስ የሚያደርገው ጨዋታ እንደመሆኑ ተጠባቂ ያደርገዋል። ወደ ሽረ አምርቶ ያለ ግብ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንድ ጨዋታ ይቀረዋል። በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ከወላይታ ድቻ ካለው አንድ ቀሪ ጨዋታ ውጭ በተከታታይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ፋሲልን በማሸነፍ እና ከባህር ዳር ከተማ አቻ በመለያየት አራት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል።

አዳማ ከተማ በሜዳው ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው ጠንካራ የማሸነፍ ሪከርድ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ሳምንታት ጀምሮ እየተሸረሸረ ይመስላል። በአማካይ ስፍራ ላይ የጉዳት ሰለባ የሚሆኑበት ተጫዋቾች መበርከታቸው ደግሞ ከተለያየ ሚና ያላቸው ተጫዋቾች በሚቆጠሩ ጎሎች ውጤት የሚሰበስበውን ቡድን እንዲቸገር አድርጎታል። አዳማ የያዘው የተጫዋቾች ስብስብ በሊጉ ከሚገኙ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የሚያደርገው እንደመሆኑ ተጫዋቾቹን በተሟላ ሁኔታ ካገኘ በሒደት ወደ ወጥ አቋሙ እንደሚመለስ ይገመታል።

በመስመር አጨዋወት ያጋደለ አጨዋወትን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተግባራዊ ሲያደርግ የታየው ሲዳማ ቡና ለመጀመርያ ጊዜ በሚያደርገው የሜዳ ውጪ ጨዋታም ተመሳሳይ አጨዋወት ይዞ እንደሚገባ ይጠበቃል። የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው አዲስ ግደይ እና ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ሐብታሙ ገዛኸኝ ላይ ያተኮሩ ረጃጅም ኳሶችም በጨዋታው ይጠበቃሉ።

ባለሜዳው አዳማ ከተማ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ከነዓን ማርክነህ፣ ቡልቻ ሹራ፣ ዐመለ ሚሊኪያስ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስን የማያሰለፍ ይሆናል። የአዲስዓለም ደሳለኝን ግልጋሎትን የማግኘቱም ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። ሲዳማ ቡና አማካዩ አበባየው ዮሀንስን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ አጥቂውን ጸጋዬ ባልቻን በጉዳት እንደማያሰልፍ ታውቋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

-በአጠቃላይ 16 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 5 ሲያሸንፍ ሲዳማ 6 አሸንፏል፡፡ በቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ አዳማ 15፤ ሲዳማ 12 ጎሎች አስቆጥሯል፡፡

-በአዳማ በተደረጉ 8 ጨዋታዎች አዳማ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ አቻ ተለያተው ሲዳማ ቡና 2 ጨዋታ አሸንፏል፡፡

-በአምና ግንኙነታቸው አዳማ ላይ 1-1 ሲለያዩ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና 1-0 ቢያሸንፍም በተጨዋች ተገቢነት ክስ በፎርፌ 3-0 በመሸነፉ ይታወሳል፡፡

-አዳማ ከተማ በ25ኛ ሳምንት ኤሌክትሪክን 6-1 ካሸነፈ በኋላ ባለፉት 7 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም፡፡ ካለፉት አምስት የሜዳው ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውም አንድ ብቻ ነው።

ዳኛ

ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው አምና በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከወልዋሎ ባደረጉት ጨወታ በወልዋሎ ቡድን መሪ ድብደባ ከደረሰበት በኋላ ከጨዋታ ርቆ የነበረው ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ 4-3-3

ሮበርት ኦዶንኮራ

አንዳርጋቸው ይላቅ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱሌይማን ሰሚድ

ሱራፌል ጌታቸው – ኢስማኤል ሳንጋሪ – አዲስ ህንፃ

በረከት ደስታ – ሙሉቀን ታሪኩ – ዳዋ ሆቴሳ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሣይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሃ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ በቀለ – ግሩም አሰፋ

ዮሴፍ ዮሀንስ – ወንድሜነህ ዓይናለም – ትርታዬ ደመቀ

ሐብታሙ ገዛኸኝ – መሐመድ ናስር – አዲስ ግደይ


ወላይታ ድቻ ከ መቐለ 70 እንደርታ

የሶዶ ስታዲየም ከመጠነኛ እድሳት መልስ በሚያስተናግደው በዚህ ጨዋታ ወላይታ ድቻ የመጀመርያ ድሉን ለማግኘት መቐለም መሪነቱን ለማጠናከር ጠንካራ ፍልሚያ ያደርጋሉ። ወላይታ ድቻ ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን አድርጎ ከሽረ አቻ ሲለያይ በሀዋሳ ከተማ ተሸንፎ ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ይሆናል። ከፋሲል ከነማ ጋር ቀሪ አንድ ጨዋታ ያላደረገው መቐለ በሜዳው ወልዋሎ እና ደደቢትን አሸንፎ በመልካም የውድድር ጅማሮ ላይ ይገኛል።

በአዳዲስ ተጫዋቾች ስብስቡን ያዋቀረው ወላይታ ድቻ ምንም እንኳን ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብን ማግኘት ባይችልም አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ወደ ራሱ ወደሚፈልገው የጨዋታ ሂደት ቡድኑን እየቀየረው መምጣቱን በተጋጣሚዎቹ ላይ እያሳየ ያለው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ማሳያ ነው። ሆኖም በማጥቃት ወረዳው ላይ ያለው ደካማ እንቅስቃሴ ውጤት ይዞ እንዳይወጣ እያደረገው ይገኛል። አዲስ ፈራሚዎቹ ባዬ ገዛኸኝ እና አንዱዓለም ንጉሴ ከቡድኑ ጋር ሲዋሀዱ የግብ ማስቆጠር ችግሩ ይቀረፋል ተብሎም ይጠበቃል።

የገብረመድህን ኃይሌው መቐለ 70 እንደርታም በተመሳሳይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚሞክር ቡድን ሲሆን በሚያጠቃበት ወቅት ሁለቱም የተለጠጡ የመስመር ተጫዋቾች ሳሙኤል ሳሊሶ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤልን ይጠቀማል። በጨዋታው ሁለቱ ፈጣን የመስመር ተጫዋቾች ብዙም ቦታቸው ከማይለቁት የድቻ የመስመር ተከላካዮች የሚጠብቃቻው ፈተና በጨዋታው ተጠባቂው ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች ብዙ የማጥቃት አማራጮች ይዘው ወደ ሜዳ ሲገቡ የታዩት መቐለዎች በዚ ጨዋታ የተጋጣሚ ቡድን የመከላካል አቀራረብ አይተው አጨዋወታቸው ታታሪው ያሬድ ከበደ ላይ ያነጣጠረ አጨዋወት ሊከተሉ እንደሚችሉም ይገመታል።

ወላይታ ድቻዎች አሁንም ኃይማኖት ወርቁን በጉዳት ሲያጡ ባዬ ገዛኸኝ በጡንቻ መሸማቀቅ ምክንያት እንዲሁም ውብሸት ክፍሌ፣ እርቅይሁን ተስፋዬን እና ተክሉ ታፈሰን በተመሳሳይ በጉዳት አያሰልፍም። ጸጋዬ ብርሀኑን ደግሞ ከጉዳት መልስ የሚያገኝ ይሆናል። በመቐለ በኩል በጉዳት ላይ  የነበሩት ኃይለአብ ኃይለስላሴ፣ አርዓዶም ገ/ህይወት እና ቢያድግልኝ ኤልያስ ከጉዳት ቢያገግሙም  ለጨዋታው ብቁ አይደሉም ተብሏል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል።  ለመጀመሪያ ጊዜ ሶዶ ላይ አምና ተጫውተው መቐለ በቢስማርክ አፖንግ ጎል 1-0 -ሲያሸንፍ በሁለተኛው ጨዋታም መቐለ 2-0 ማሸነፍ ችሏል።

– ወላይታ ድቻ ያለፉት አራት ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያልቻለ ሲሆን መቐለም በአራት ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግዷል።

ዳኛ

ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ኢሳይያስ ታደሰ በዋና ዳኝነት እንዲመሩት ተመድበዋል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

ያሬድ ዳዊት – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኄኖክ አርፊጮ

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – ፀጋዬ አበራ – ፍጹም ተፈሪ – ኄኖክ ኢሳይያስ

አንዱዓለም ንጉሴ

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ -አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ-አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

አማኑኤል ገ/ሚካኤል – ኃይደር ሸረፋ – ሳሙኤል ሳሊሶ

ያሬድ ከበደ


ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

አዲስ አዳጊው ባህር ዳር ከተማ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደርጋል። ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጭ አድርጎ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ከሲዳማ ቡና ነጥብ በመጋራት ድንቅ አጀማመር ያደረገው ባህር ዳር ከስሑል ሽረ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው ወልዋሎ እና ወላይታ ድቻን ሲያሸንፍ ከሜዳው ውጪ በአወዛጋቢ ዳኝነት በታጀበው ጨዋታ በፋሲል ከነማ ተሸንፏል።

2008 በኋላ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ የሚያስተናግደው የባህር ዳር ስታድየም ሁለት ተመሳሳይ የመስመር ላይ አጨዋወት የሚከተሉ ቡድኖችን የሚያሳይ እንደሚሆን ቡድኖች ቀደም ብለው ባደረጉት ጨዋታ ለመመልከት ችለናል። የጣና ሞገዶቹ በተለይ በፈጣኑ የመስመር አጥቂ ግርማ ዲሳሳ ላይ ትኩረት ያደረገ አጨዋወትን ሲከተሉ የወሰኑ ዓሊ እና የፍቃዱ ወርቁ የሚዋልል እንቅስቃሴ ለሀዋሳ የተከላካይ ክፍል ስጋት ይሆናሉ። በ2009 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ መከላከያን ከረታ በኃላ ተከታታይ 21 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያልቻለው ሀዋሳ ከተማ በአዲሴ ካሳ መመራት ከጀመረ ወዲህ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ወደ ቀጥተኛ አጨዋወት መቀየሩ ከሜዳ ውጪ ያለውን ድክመት ለማሻሻል እንደሚረዳው ይጠበቃል። የመስመር ተከላካዮቹ የተሳኩ ተሻጋሪ ኳሶች እና ከታፈሰ ሰለሞን የሚላኩ የመጨረሻ ኳስ አቅርቦትን በእስራኤል እሸቱ የሚመራው የሀዋሳ ከተማ የአጥቂ ክፍል በአግባቡ ከተጠቀመ ለአዲስ አዳጊዎቹ ፈተና መሆን እንደሚችሉ ይገመታል።

ማራኪ ወርቁ እና እንዳለ ደባልቄን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ባህርዳር ከተማ አጥቂው ጃኮ አራፋት እና ጋናዊው ተከላካይ አሌክስ አሙዙ የወረቀት ጉዳዮች በመጠናቀቃቸው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነውለታል ተብሏል። አምና በከፍተኛ ሊጉ ቅጣት የተጣለበት ዳግማዊ ሙሉጌታ አሁንም ለዚህ ጨዋታ የማይደርስ ይሆናል። በሀዋሳ በኩል አዳነ ግርማ እና አዲሱ አይቮሪኮስታዊ የግራ መስመር ተከላካይ ያኦ ኦሊቨር በቀይ ካርድ ቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። ሶሆሆ ሜንሳህ ከመጠነኛ ጉዳት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ይህ ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸው ነው። ሀዋሳ ከተማም በ2000 ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ከገጠመ ከ11 ዓመት በኋላ ሌላኛውን የባህር ዳር ቡድን የሚገጥም ይሆናል።

ዳኛ

ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ በመሀል ዳኝነት እንዲመራ ተመድቧል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ 

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ደስታ ዮሀንስ

አስጨናቂ ሉቃስ – መሳይ ጳውሎስ

ፀጋአብ ዮሴፍ – ታፈሰ ሰለሞን – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን

እስራኤል እሸቱ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ሳምላምላክ ተገኝ – አሌክስ አሙዙ – ወንድሜነህ ደረጀ – አስናቀ ሞገስ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ዳንኤል ኃይሉ – ኤልያስ አህመድ

ግርማ ዲሳሳ – ወሰኑ ዓሊ – ፍቃዱ ወርቁ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ስሑል ሽረ

በቴዎድሮስ ታከለ እና ዳዊት ጸኃዬ

በውድድር ዓመቱ ጅማሮ ፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝ ማኑኤል ቫስ ፒንቶን ካሰናበተ በኃላ በምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ መሪነት ሊጉን የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ 1 ለ 0 በመሸነፍ ጉዞውን ከጀመረ በኋላ አዲሱ እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ጆን ስቲዋርት ሀልን በመሾም ዝግጅታቸውን እያደረጉ የቆዩ ቢሆንም ለብሔራዊ ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን በማስመረጣቸው ምክንያት ከአዳማ እና ጅማ አባ ጅፋር ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ጨዋታ በተስተካካይ መርሀ ግብር ተይዞለት ነው የዛሬውን የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ የሚያደርገው። በአንፃሩ ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጭ በመውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን በሜዳው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያለ ጎል አቻ ተለያይቶ ቀሪ አንድ ጨዋታ ከባህርዳር እየቀረው በአራተኛው ሳምንት ትልቁን የሀገሪቱን ክለብ የሚገጥም ይሆናል።

ፈረሰኞቹ በመጀመሪያ ጨዋታ ላይ በአስገራሚ መልኩ በሁለት አጥቂዎች እንዲሁም ከእነሱ ጀርባ ሶስት የአጥቂ አማካዮችን አሰልፈው የነበረ ቢሆንም በ90 ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ አንድ ብቻ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ብቻ ነበር ማድረግ የቻሉት። በዚህም አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ምንም እንኳን ቡድኑን ከተረከቡ ጥቂት ጊዜያትን ብቻ ቢያስቆጥሩም በተለይም ቡድኑ በማጥቃት አጨዋወት ወቅት የሚታይበትን ክፍተት መቅረፍ ተቀዳሚ የቤት ስራቸው ይሆናል። ምንም እንኳን የመጀመሪያ የፉክክር ጨዋታቸው ቢሆንም በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ በመጀመሪያ 11ተሰላፊነት ጨዋታውን ጀምረው ከነበሩት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች መካከል ሦስቱ ካሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ አንጻር አዲሱ የፈረሰኞቹ አለቃ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ያወርዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳቸው ውጭ የሚጫወቱት ሽረዎች ከሜዳ ውጪ የሚኖራቸውን አቀራረብ ለመተንበይ ቢከብድም ባለፉት ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት የሚሞክሩ ሲሆን በዚህ ጨዋታ ግን እንደተጋጣሚያቸው ክብደት በሁለትመከላከል ባህርይ ያላቸው አማካዮች የተዋቀረ ቡድን ይዘው ሊገቡ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል። በተጨማሪ ምንም እንኳን በሁለት ጨዋታ ግብ ባያስተናግድም ገል ማስቆጠር ያልቻለው ሽረ ከርቀት ከሚሞከሩ ኳሶች ባሻገር የጠሩ የግብ እድሎችን የመፍጠር ችግሩን በምን መልኩ ይቀርፋል የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።

ፈረሰኞቹ አሁንም ወሳኝ የተባሉ ተጫዋቾችን በጉዳት ያጣል። ረጅም ጊዜን ከጉዳት ርቆ የቆየው ሳላሀዲን ሰዒድ እንዲሁም ጌታነህ ከበደ እና መሀሪ መና ምንም እንኳን ሶስቱም ከጉዳት ቢያገግሙም ከጨዋታው ውጭ መሆናቸው እርግጥ ሆኗል። ከስሑል ሽረ በኩል ንስሃ ታፈሰ፣ ሸዊት ዮሀንስ እና ግብ ጠባቂው ሐፍቶም ቢሰጠኝ በጉዳት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

ሁለቱ ክለቦች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲገናኙ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነታቸው ሆኖ ይመዘገባል።

ዳኛ

ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊጉ ካደጉ ዳኞች መካከል አንዱ የሆነው ፌዴራል ዳኛ ብርሀኑ መኩሪያ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

አብዱልከሪም መሐመድ – አስቻለው ታመነ -ምንተስኖት አዳነ – ኄኖክ አዱኛ

ጋዲሳ መብራቴ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ

በኃይሉ አሰፋ – አሜ መሐመድ – አቤል ያለው

ስሑል ሽረ (4-3-3)

ሰንዴይ ሮቲሚ

በረከት ዘላለም – ሙሉጌታ አንዶም – ዴሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ

ኄኖክ ካሳሁን – ደሳለኝ ደባሽ – ሰለሞን ገብረመድህን

ልደቱ ለማ – ሚድ ፎፋና – ኢብራሂማ ፎፋና