የአሰልጣኞች አስተያየት – ወልዋሎ 1-0 ደቡብ ፖሊስ 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ዛሬ መደረግ ሲጀምር በመቐለው ትግራይ ስታድየም ደቡብ ፖሊስን ያስተናገደው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 1-0 አሸንፏል። የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል። 


” በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለን እንደመምጣታችን ውጤቱ ጥሩ ነው” ጸጋዬ ኪዳነማርያም

የዛሬ ጨዋታ ከባድ ነበር። ደቡብ ፖሊስ በሊጉ የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የያዘ ቡድን ነው። ከዛ በተጨማሪ የኛ ቡድን ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥሎ ስለመጣ ጫና ውስጥ ሆነን ነው የተጫወትነው። እንደ ቡድን ብዙ ለውጦች አድርገን ነው ወደዚ ጨዋታ የቀረብነው፤ ተከላካይ ክፍላችን ከባለፉት ጨዋታዎች በተለየ ጠንካራ ነበር። ከዛ ውጪ የማጥቃት ኃይላችን ጥሩ ነበር፤ በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ ብዙ የጎል እድሎች ፈጥረናል። በአጠቃላይ ስናየው ግን የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለን እንደመምጣታችን ውጤቱ ጥሩ ነው። ለቀጣይ ጨዋታዎቻችን ጥሩ የሞራል ስንቅ ይሆነናል። በዛሬው ጨዋታ ዘጠና ደቂቃ ሙሉ ድጋፍ ለሰጡን የወልዋሎ እና መቐለ ደጋፊዎችም ማመስገን እፈልጋለው።


“ብንሸነፍም ቡድናችን ከለፉት ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይቷል” ዘላለለም ሽፈራው – ደቡብ ፖሊስ

ጨዋታው በተወሰነ መልኩ ጥሩ ነበር። ቡድናችን ቢሸነፍም ከወትሮው ተጭኖ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል። ያለፉት ጨዋታዎች ከነበረን ብቃት ስናስተያየው ዛሬ የተሻልን ነበርን። በርግጥ በመጀመርያው አጋማሽ በተከላካዮቻችን ላይ የመረጋጋት እና ተቀናጅቶ የመጫወት ችግሮች ነበሩ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ያንን ችግር ቀርፈው ገብተዋል። ሌላው የዛሬ ድክመታችን የማጥቃት ኃይላችን ትንሽ ተገድቦ ነበር። ከዛ ውጭ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገናል።

መቐለ ስመጣ የመጀመርያዬ አይደለም። ከ1993 ጀምሮ በተለያየ መንገድ መጥቻለው። ደጋፊው ድሮ እንደማቀው ነው፤ ጥሩ ለተጫወተ ነው የሚያጨበጭበው። እንዳየኸው ቡድናችን ተሸንፎ ሲወጣ አይዞህ እያሉን ነበር እና ሁኔታው ለኔ አዲስ አይደለም። እንደጠበቅኩት ነው፤ ጨዋ ደጋፊ ነው።