ጅማ አባጅፋር ከናና ሰርቪስ ጋር የዲጂታል ሲሰተም ስራ ስምምነት ተፈራረመ 

የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባጅፋር ናና ሰርቪስ ከተባለ የዲጂታል ሲስተም ድርጅት ጋር የስራ ውል ስምምነት መፈፀሙን አስታውቋል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ዳምጠው ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ ክለቡን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለው ይህ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስራ ስምምነት የደጋፊ ምዝገባን ጨምሮ ለማልያ እና ቁሳቁስ ግዢ እንዲሁም የአባልነት መዋጮ እና የተለያዩ ክፍያዎችን በዲጂታል መንገድ ለመፈፀም ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ ወርሀዊ እና ዓመታዊ የኮከብ ተጫዋቾች ምርጫን ለመምረጥ እንዲሁም በክለቡ ዙርያ የተለያዩ ዜናዎችን እና መረጃዎችን በቀላሉ ለደጋፊው የሚያቀርብ የዲጅታል ሲስተም ነው ተብሏል። 

ዛሬ ስምምነቱን የድርጅቱ ተወካይ እና የክለቡ ስራ አስኪያጁ አቶ እስከዳር በፅህፈት ቤት የተፈራረሙ ሲሆን ሲሆን ክለቡን በፋይናንስ ረገድ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። በተለይ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት ወደተጠቃሚ ከሚደርሰው መረጃ ገቢ ክለቡ 80 በመቶ፣ ድርጅቱ ደግሞ 20 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተገልጿል። 

ሌላው የፕሪምየር ሊግ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ዓመት መጨረሻ ዕልባት ከተሰኘ የዲጂታል ፋይናንሻል ሲስተም ኩባንያ ጋር መስራት መጀመሩ የሚታወስ ነው።