ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ድል አሳክቷል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አዲስ አዳጊው ስሑል ሽረን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ ስቲዋርት ሃል እየተመራ 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ አሳክቷል ፤ ተቀይሮ የገባው አቤል ያለውም ደምቆ አምሽቷል፡፡

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በባህርዳር ከተማ ከተረታው ስብስብ ውስጥ ጌታነህ ከበደን አቡበከር ሳኒ እንዲሁም አማካዮቹን ካሲም ታይሰናን እና ጋዲሳ መብራቴን በአስቻለው ታመነ እና ናትናኤል ዘለቀ ቀይረው የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል፡፡ በአንጻሩ ስሑል ሽረዎች ከአዳማ ጋር አቻ ከተለያየው ቡድን ውስጥ ሳሙኤል ተስፋዬን ፣ ሸዊት ዮሀንስ እና ልደቱ ለማን አስወጥተው በደሳለኝ ደባሽ ፣ ጅላሎ ሻፊ እና ኪዳኔ አሰፋ ተክተው ነበር የጀመሩት፡፡ በአዲሱ እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ስቲዋርት ሃል እየተመሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዛሬው ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከዚህ ቀደም ይታወቁበት በነበሩት አጨዋወት ማለትም ኳሶችን በፍጥነት ወደ መስመር በማውጣት ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ አድርገዋል፡፡ በተደጋጋሚ በረጅሙ በሚላኩ ኳሶች ከሽረ ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተት ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡


እምብዛም የግብ ሙከራዎች ባልነበሩት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አንጻራዊ የበላይነት በነበረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ በ25ኛው ደቂቃ ናትናኤል ዘለቀ በረጅሙ ከሽረ ተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ አሜ መሀመድ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላ የስሁል ሽረው የመሀል አማካይ ደሳለኝ ደባሽ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። ጊዮርጊሶች መሪ ከሆኑ በኋላ በነበሩት ጥቂት ደቂቃ ሽረዎች በሁለት አጋጣሚዎች በጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ በርከት ብለው ቢገኙም ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር ግን አልቻሉም። በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1-0 የበላይነት ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል፡፡


በ49ኛው ደቂቃ የሽረው ተከላካይ ሙሉጌታ አንዶም ከመሀል ሜዳ የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ሚዶ ፎፋና የጊዮርጊሱን ግብጠባቂ አልፎ ለማስቆጠር ቢሞክርም እንደምንም ብሎ ማታሲ አድኖበታል። በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ይበልጥ ተሽለው በቀረቡት ጊዮርጊሶች በኩል በ65ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረው ኳስ ተጨራርፎ ሲደርሰው ሁለተኛው ቋሚ አቅራቢያ ይገኝ የነበረው ምንተስኖት አዳነ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ከናትናኤል ዘለቀ እና ከተከላካዩ ፊሪምፖንግ ሚንሳህ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ሽረዎችን ማስጨነቃቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ለክለቡ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው አቤል ያለው በ83ኛው ደቂቃ ላይ ከሽረው የመሀል ተከላካይ ዘላለም በረከት የነጠቀውን ኳስ በሰንደይ ሮቲሚ አናት ላይ በማሳለፍ ሦስተኛዋን ግብ በማራኪ መልኩ አስቆጥሯል። በተመሳሳይ በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው አቤል ያለው በ93ኛው ደቂቃ ኄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር በረጅሙ ወደ ግራ ያሻገረውን ኳስ አብዱልከሪም መሀመድ ተቆጣጥሮ ሲያቀብለው አቤል በቀላሉ ለቡድኑ አራተኛ ለርሱ ደግሞ ሁለተኛ የሆነችውን የማሳረጊያ ጎል ከመረብ አገናኝቷል።


በዚህም ውጤት መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ሲያገኝ ሽረዎች ደግሞ ከሦስት ጨዋታ በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል፡፡


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ ፡LINK