የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ዛሬ ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የአዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መርሐ ግብር በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኞቹ የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል። 

“አንድ ስህተት ነው ዋጋ ያስከፈለን” ሲሳይ አብርሃ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታውን ብልጫ በወሰድንበት የመጀመርያ አጋማሽ ላይ ጨርሰን መውጣት ነበረብን። እነሱ  ወደ እኛ የሜዳ ክፍል የመጡበት አጋጣሚ አልነበረም። አንድ ስህተት አገኙ፤ እሱንም ማስቆጠር ቻሉ እንጂ እኛ የተሻልን ነበርን። የእግርኳስ አንዱ አካል ነው። እንደ አሰልጣኝ በውጤቱ ብከፋም ተጫዋቾቻችን ጥሩ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ መዳከም 

ድካም አልነበረም፤ የትኩረት ማጣት እንጂ። ጎል ሲቆጠረብህ የሚመጣ የስነ ልቦና ችግር ነው። እኛ ስንት ጊዜ ወደ ፊት ሄደናል፤ ተጫዋቾቼም የተሻለ ነገር ለመስራት ዘጠናውን ደቂቃ ታግለዋል። እንዳልኩት አንድ ስህተት ነው ዋጋ ያስከፈለን። ወደ ፊት እየቀረፍነው የምንሄደው ነገር ነው።

ከአሸናፊነት መራቅ እና ከሜዳ ውጪ ጉዳዮች

ምንም ነገር የለም፤ ያው እግርኳስ ነው። እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል። ዛሬ የሆነ ነገር አቅደህ ትገባለህ ሳይሳካ ይቀራል። ነገ ደግሞ ሌላ የተሻለ ነገር ለመስራት አቅደህ ትመጣለህ። እግርኳስ ሁሌ ስህተት ይኖረዋል። አሁን ምንም ማለት አይቻልም፤ ነገ የተሻለ ነገር ይዞ ለመምጣት እንሰራለን።

ደጋፊውን ደስተኛ ያላደረገው የተጫዋቾች ቅያሪ

ተመልካች እንደዛ ሊያስብ ይችላል። እኛ ያደረግነው የታክቲክ ለውጥ ነው።  ከ4-3-3 ወደ 4-4-2 ለመቀየርና ሱራፌልን ወደ ኋላ በማድረግ ወደ ፊትም ስለሚሄድ ዱላን እያገዘው መስመር ላይ የቁጥር ብልጫ ወስደን ጎሎችን ለማስቆጠር ነበር ይሄን ያደረግነው።

“ለእኛ ጨዋታው መልካም ነበር” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና 

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው ለእኛ በጣም ከባድ ነበር። ግብ ጠባቂው መሣይ አያኖ እዚህ ከመጣን በኋላ ነበር የተጎዳብን። ተጫዋቾቼ የአዳማ አየር ከብዷቸው ነበር። እኔ ስጫወት እንደማውቀው አይደለም፤ የአዳማ አየር በጣም ተለውጧል። ያም ቢሆን ቀስ እያሉ እየተላመዱ ሲመጡ የተወሰደባቸውን ብልጫ መቆጣጠር ችለዋል። ከእረፍት መልስ በተለይ ብልጫ ወስደን መጫወት ችለናል። ለእኛ ጨዋታው መልካም ነበር ።

የተጫዋች ቅያሪ 

ከእረፍት በፊት መሀል ሜዳ ላይ ብልጫ ተወስዶብን ነበር። ይሄን ለማስተካከል ዮሴፍን በማስገባት ያደረግነው ቅያሪ ተሳክቶልን ከእረፍት በኋላ ብልጫ መውሰድ ችለናል። ዮሴፍ በብሔራዊ ቡድን አገልግሎት ድካም ላይ ስለነበር እረፍት አድርጎ ሁለተኛው ግማሽ ላይ እንዲገባ አስበን ነው ይህን ያደረግነው ።