የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 መቐለ 70 እንደርታ

በወላይታ ድቻ እና መቐለ 70 እንደርታ መካከል ከተደረገው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ገልፀዋል።

“የተሻልን ስለነበርን ውጤት ይዘን ልንወጣ ችለናል”  ዘነበ ፍስሀ – ወላይታ ድቻ 

“ካለፈው ጨዋታ ተነስን ነው በተጫዋቾቼ ላይ ለውጥ ያደረግነው። ትንሽ የቅንጅት ችግር ነበር፤ በተወሰኑ መልኩ መሻሻሎች አሉ። ከባለፈው ጨዋታ ዛሬ በሚገባ የተሻለ ነው። ጥሩ መነሳሳት እና መነቃቃት አለ። አሁንም ቢሆን ይቀረናል፤ ከዚህ የበለጠ መሻሻል አለብን። መቐለ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። ስለዚህ እኛም እኛም የነሱን አጨዋወት አይተን የተሻልን ሆነን ውጤት ይዘን ለመውጣት ነበር የገባነው፤ ተሳክቶልናል። በጣም ደስ ብሎኛል።”

የመሀል ሜዳ ብልጫን በማጥቃቱ ላይ ያለመድገም ችግር

አሁን የኔ ፍላጎት ኳሱን መቆጣጠር እና ብዙ ቅብብል ማደረግ ነው። ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ኳስን መሠረት አድርገው እንዲጫወቱ ነው የኔ ፍላጎት። በዚህ ሂደት ደግሞ በተቻለ መጠን የተቃራኒ ቡድን ጋር መድረስ አለብን። በዚህም ስራ ላይ በይበልጥ እየሰራን ነው። ቢሆንም አሁን ላይ ችግሩ ተጫዋቾቹ ከተለያየ ቡድን ነው የመጡት። 11 ተጫዋቾች አዲስ ናቸው፤ በሚገባ ለማዋሀድ ጊዜ እየወሰደብኝ ነው። ችግራችን አሁንም መቆራረጥ ይታያል፤ ፊት ላይ ይህን ችግር እየቀረፍን እስከ መጨረሻው በአሸናፊነት መዝለቅ እንፈልጋለን. እስካሁን የመጀመርያ 11 ተጫዋቾችን ለማግኘት ስሞካክር ነበር። አሁን ግን በሚገባ ቋሚ ተሰላፊዎቼን እያገኘሁ ነው። 

“ሜዳው ለመጫወት ምቹ አይደለም” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

“ለኔ ጨዋታው ከባድ ነው፤ ይህን ስል በዚህ ሜዳ ላይ እግርኳስ ለመጫወት ምቹ አይደለም። በተለይ ኳስ ለመቆጣጠር ለሚያስብም ቡድን. ከዚህ በተረፈ ጨዋታው በጣም ደስ የሚል ሰላማዊ ጨዋታ ነው። ነገር ግን እንዲህ ሰላማዊ ጨዋታ እየተደረገ ተጫዋቾች በሰላም እየተጫወቱ ዳኞች ለምን እንደሚሸበሩ አይገባኝም። ዝም ብለው መረበሽ ደሞ የለባቸውም፤ ከዚህ መውጣት መቻል አለባቸው። በአጠቃላይ ግን ህዝቡ፣ መንፈሱ፣ ድባቡ ጥሩ ነው። በዚህ ጨዋታ በፍፁም ተጫዋቾቼን መተቸትም ብዙም መናገር  አልችልም። ለምን ሜዳው አመቺ ስላልሆነ ኳሱን መለጋት፣ መመለስ ካልሆነ በስተቀር የራስህን አጨዋወት መተግበር አትችልም፡፡ በቀጣይ ግን ተስተካካይ ጨዋታም ስላለን የተሻለ ነገር ይኖረናል ብለን እናስባለን ፡፡”