የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

ከዛሬዎቹ የፕሪምየት ሊጉ ጨዋታዎች መካከል ጎንደር ላይ በፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የተደረገው  ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል። የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞችም ስለጨዋታው ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል። 

“በሁለተኛው አጋማሽ ከነበረን እንቅስቃሴ አንፃር አቻ መውጣታችን ተገቢ ነው” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ 

ስለ ጨዋታው…

“የጨዋታ ውጤት ከሦስቱ አንዱ ነው ፤ ማሸነፍ ፣ መሸነፍ እና አቻ መውጣት። ወደ ሜዳ የገባነው ለማሸነፋ ነው። በሁለተኛው አጋማሽ ከነበረን እንቅስቃሴ አንፃር አቻ መውጣታችን ተገቢ ነው።  የማጥቃት ክፍላችን ላይ አለመረጋጋት ይታይ ነበር። እናም እንደዛ እየተንቀሳቀስን ግብ ማስቆጠር ይከብዳል። በመሆኑም እዛ ላይ መስራት ይጠበቅብናል ።”

ስለ ተጋጣሚ አቀራረብ…

“በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወደኋላ አዘንብለው ነበር የሚጫወቱት። አቻ መውጣቱን ፈልገውት ነበር። እናም ወደ ኋላ አዘንብለው በሚጫወቱ ሰዓት ረጃጅም ኳሶች ስንጠቀም ለነሱ ነበር ምንሰጣቸው።  አቻ ለመውጣችን አንዱ ምክንያትም ይህ ነበር ።”

” ባገኝነው ነጥብ ደስተኛ ነኝ ” ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

” ጥሩ አልነበርንም ቢሆንም ግን ከፋሲል አንድ ነጥብ መውሰድ ችለናል። ፋሲል ጥሩ ነበር። ባገኝነው ነጥብ ደስተኛ ነኝ። ግን ከዚህ በላይ  ማድረግ እንችል ነበር።  ጥሩዉ ነገር ግብ አለማስተናገዳችን ነው። ይህን ለወደፊት እንደ ጥሩ ነገር ነው ማየው። ሆኖም ከዚህም በላይ ጥሩ መስራት እንችላለን። በአካል ብቃት እና በቴክኒክ ክህሎት የተሻለን መሆን አለብን።  ለምሳሌ ከአልሃሰን ካሉሻ  የተሻለ ብቃት ማግኝት መቻል አለብን። እንደ ወድድር ዓመት መጀመሪያ ሁለት አሸንፈን ከፋሲል ጋር ነጥብ በመጋራታችን ግን አልከፋኝም። እንዲያው ረክቻለሁ። ”

የተጫዋቾች ጉዳት የአካል ብቃት ጥያቄን ያስነሳ እንደሆን..

” የአካል ብቃት ማነስ አይደለም። የነሱ አጥቂዎች ትልልቆች መሆናቸው ነው። እኛ በቀጣይ በጣም ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታዎችን ያማከለ ልምምድ እንሰራለን። ያገጠሙንም ጉዳቶች ቀለል ያሉ  ናቸው። ለምሳሌ  አህመድ ረሺድ ፊቱ ላይ ነው የተገጎዳው። እናም ይሄ ለኛ ትምህርት ነው። “