ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | መከላከያ አሁንም ከቅድመ ማጣሪያው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል

በ2018/19 ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከናይጄሪያው ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው መከላከያ በድምር ውጤት 5ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል። 

በጨዋታው መከላከያዎች ናይጄርያ 2-0 ከተሸነፈው ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ተመስገን ገብረኪዳንን በፍፁም ገብረማርያም በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ የሬንጀርስ ተከላካይ ሴሙ አብዱል በግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጁ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሮ መከላከያ ድምር ውጤቱን እንዲያጠብ እና ውጤቱን ለመቀልበስ የሚያግዝ አጀማመር እንዲያደርግ አድርጓል፡፡

በግቧ የተነቃቁ የሚመስሉት መከላከያዎች ኳስን ተቆጣረው በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ግን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የነበረው መነሳሳት በሂደት ተቀዛቅዞ ታይቷል፡፡በ33ኛው ደቂቃ ላይም የሬንጀርሱ የግራ መስመር ተከላካይ ሲያሻማ ብራይት ሲላስ በግሩም አጨራረስ እንግዳውን ቡድን አቻ አድርጎ የድምር ውጤቱን ልዩነት መልሶ አስፍቷል።

በተመሳሳይ በ39ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ግብ ካገኙ በኃላ ተወስዶባቸው የነበረውን የጨዋታ ብልጫ መልሰው ማግኘት የቻሉት ሬንጀርሶች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በፈጣን ሽግግር የተገኘችውን ኳስ ወደ መከላከያ የግብ ክልል ይዘው ሲገቡ ሽመልስ ተገኝ በጎድዊን አጉዳ ላይ ጥፋት በመስራቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት የመስመር አጥቂያቸው ጎድዊን አጉዳ ራሱ አስቆጥሮ ቡድኑን ከመመራት ተነስቶ ወደ መሪነት እንዲሸጋገር ረድቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የ2ለ1መሪነትን ይዞ ወደ ሜዳ የተመለሰው ሬንጀርስ ከመጀመሪያው በተሻለ አደገኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችሏል፡፡ በአንጻሩ ጨዋታውን አሸንፈው ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ አራት ግቦችን ማስቆጠር ይጠበቅባቸው የነበሩት መከላከያዎች በቁጥር በርከት ብለው በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ላይ ቢገኙም የሬንጀርስን የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመርያ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ከተገኘችውንና የሬንጀርሱ ግብጠባቂ በግሩም ሁኔታ ካዳነበት ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርቷል፡፡

 

በ77ኛው ደቂቃ ላይ እንግዳዎቹ ሬንጀርሶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ኪቨን ኢቶያ ወደ ግብ ሲልካት በመከላከያ ተጫዋቾች ተጨርፋ የጦሩን ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ህልምን ገደል የከተተች የማሳረጊያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በዛሬው ጨዋታ 3ለ1 ማሸነፍ የቻሉት ሬንጀርስ ኢንተርናሽናሎች በድምር ውጤት 5-1 በማሸነፍ ወደ አንደኛው ዙር ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ በአንፃሩ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው በአራት ዓመታት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ መሳተፍ የቻለው መከላከያ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ከቅድመ ማጣርያው ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ ፡ LINK