የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-3 ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም የናይጄሪያው ሪንጀርስ ኢንተርናሽናል ያስተናገደው መከላከያ 3ለ1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“እኛ በአላማ ነበር የምንጫወተው ፤ እነሱ ኳሱን በመያዝ ላይ ብቻ ነበር የተጠመዱት”- ኢማማ አማፓክቦ 

ስለ ጨዋታው

“ጥሩ የሚባል ጨዋታ ነበር፤ ማሸነፍ ችለናል። ይህ ማለት ግን መከላከያ መጥፎ ቡድን ነው ማለት አይደለም። ልዩነቱ የነበረው እኛ ያገኘናቸውን እድሎች መጠቀም መቻላችን ነበር፡፡ ወደ እዚህ የመጣነው ላለመሸነፍ፤ ግብ ቀድመን አስቆጥረን እነሱ ላይ ጨዋታውን ለማክበድ አስበን ነበር፡፡”

ጨዋታውን ስለቀየረው አጋጣሚ

” እነሱ ጨዋታው በተጀመረባቸው ደቂቃዎች ግብ ማግኘታቸው ጨዋታውን ከባድ አድርጎብን ነበር። ነገርግን የመጀመሪያ ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ተጨማሪ ግቦች ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። እኛም ይሄን ለመጠቀም ሞክን ማድረግ ችለናል፡፡”

ስለ መከላከያ

“መጥፎ የሚባል ቡድን አይደለም፤ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ከእነሱ በተሻለ በአላማ ነበር የምንጫወተው ። እነሱ ኳሱን በመያዝ ላይ ብቻ ነበር የተጠመዱት። በአንጻሩ እኛ ኳሱን ስንይዝ በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ እንጫወት ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ በጣም ጥሩ ቡድን ናቸው። በዚህ ቡድን ላይ ሁለት ሶስት ልምድና ብስለት ያላቸው ተጫዋቾች ቢጨመሩ ብዙ ርቀት መጓዝ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለረጅም ጊዜ አብረው የቆዩ ነው የሚመስሉት። የአሰልጣኙን የአጨዋወት ፍልስፍና በጥሩ መልኩ ተረድተዋል፡፡ ነገርግን ጥሩ ጨዋታ የሚባለው ጥሩ ተጫውተህ ማሸነፍ ስትችል ነው ፤ ኳሱን ስትቆጣጠር ወደ ጎል መድረስ አላማህ መሆን አለበት፡፡”

“የዛሬው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ እንደጠበቅነው አልነበረም”- ሥዩም ከበደ

ስለ ጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ እንደጠበቅነው አልነበረም፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ የነበረን እንቅስቃሴ ከዚህ የተሻለ ነበር፤ በተቃራኒው እነሱ ደግሞ ሜዳቸው ላይ ካደረጉት በተለየ እዚህ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ በተንቀሳቀስነው መልክ መቀጠል ሲገባን በተለይ ካገባን በኃላ እነሱም በአየር ሁኔታው እንደተቸገሩ እያየን ያንን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ሲገባን ያንን ማድረግ አልቻልንም፡፡የመጀመሪያ ጎል ቀድመን ብናገኝም በሂደት የኛ ልጆች መረጋጋት ባለመቻላቸው በታክቲኩ ረገድ እነሱ ከኛ ተሽለው መገኘት ችለዋል፡፡ በዛሬው ጨዋታ እነሱ ከመጀመሪያው ጨዋታ በተለየ በብዛት ወደ ጎል መድረስ ችለዋል ፤ በአጠቃላይ በብዙ መስፈሮቶች ከእኛ ተሽለው በመገኘታቸው አሸንፈውናል፡፡”

በመጀመሪያው ደቂቃ ግብ ስለማስቆጠራቸው 

“ለጨዋታው ባደረግነው ዝግጅታችን ላይ የተነጋገርነው ይህን ስለማድረግ ነበር፤ ያንን ማድረጋችን ያነሳሳናል ብዬ አስቤም ነበር። እነሱም በተመሳሳይ ያንን በማድረግ ጨዋታውን ሊያከብዱብን ይችላሉ የሚል ስጋት ነበረኝ። ነገርግን እኛ ያንን ማስቀጠል አልቻልንም፡፡ አላስፈላጊና የተቆራረጡ አጫጭር ኳሶች ፤ የአጥቂዎቻችን በወጥነት አለመንቀሳቀስ ነገሮችን አበላሽተውብናል፡፡”