በአንድ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ላይ የቀን ለውጥ ተደረገ

የመርሐ ግብር ማስተካከያ በማያጣው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል በአንዱ ላይ ሽግሽግ ተደርጎበታል፡፡

በነገው ዕለት በመከላከያ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ወደ ሰኞ ተሸጋግሯል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው መረጃ መሠረት ጨዋታው የተሸጋገረው ዓመታዊው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ስታድየም የሚከበር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጨዋው ሰኞ ታኅሳስ 1 ቀን 2011 በአዲስ አበባ ስታድየም 11፡00 ላይ የሚከናወን ሲሆን በተመሳሳይ ነገ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሊደረግ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ሰኞ 09፡00 ላይ ይደረጋል፡፡ እሁድ የሚደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ግን በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

በተያያዘ ዛሬ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሊካሄድ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጥረት ኮርፖሬት ጨዋታ ለነገው በዓል ቅድመ ዝግጅት በስታድየሙ የሚከናወን በመሆኑ ቦሌ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ በ10፡00 የሚደረግ ይሆናል፡፡