የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው ሀዋሳ ላይ ገጥሞ 2 ለ 1 ማሸነፍ ከቻለ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል። 

“በቡድኔ በጣም ኮርቻለሁ” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ጥሩ እና ተመጣጣኝ ነበር። በተለይ የመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃ የተመጣጠነ ነበር። ከዛ በኃላ ባሉት ግን ጎሉን ካገባን በኃላ ብልጫዎች ነበሩን። ከእረፍት መልስም ያለንን አስጠብቀን ግብም በማግባት የተሻለ እንቅስቃሴን አድርገናል። ዞሮ ዞሮ በሰራነው ስህተት ጎል ቢቆጠርብንም በቡድኔ በጣም ኮርቻለሁ። ደስ ብሎኛል”

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ማሸነፍ

“ብዙ አሰልጣኞች ሲዳማ ቡናን አሰልጥነዋል። በኔ የአሰልጣኝነት ዘመን ይህ መጥፎ ታሪክ መነሳቱ እና መሰበሩ ደስ ብሎኛል። መጀመሪያም ስፈልገው የነበረውን ነገር በማየቴ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ግን ጊዮርጊስን አሸነፍን ማለት ጨዋታውን ጨረስን ማለት አይደለም፤ ጊዮርጊስ እንደሌሎች ተጋጣሚ ቡድኖች ነው የምናየው። ጠንካራ ቡድን ቢሆንም ከዚህ በኃላም ብዙ ስራ ይጠብቀናል። ቡድናችንን ጠንካራ ለማድረግ ጠንክረን እንሰራለን። ከዛ ባለፈ ግን ጊዮርጊስን በማሸነፋችን አንድ ደረጃ ወደ ፊት ሄደናል። በዚህም ደስተኛ ነኝ”

የጎል ምንጮቹ የመስመር ተጫዋቾቹ ብቻ መሆን 

“እኔ ከዚህ ሀሳብ በተቃራኒው ነኝ። የአጥቂ ችግር የለብንም፤ ምክንያቱም ፀጋዬ ባልቻ ዛሬ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አዲስ ግደይ በነፃነት እንዲጫወት ነው ያደረገው። እንደ ሙያተኛ ቡድኔ በአዲስ ግደይ ትከሻ ላይ መሆኑ ሳይሆን አዲስ  ራሱ ያመጣው እንቅስቃሴ ተፅእኖ መፍጠሩ ነው። ቡድኔ በአዲስ የተመረኮዘ አይደለም። ለአዲስ ኳስን የሚሰጡት አጥቂዎች እና የመስመር ተጫዋቾች ናቸው። ስለዚህ የአጥቂ ችግር ቡድኑ ላይ የለም፤ ክፍተትም ካለም ለማሻሻል ጠንክረን እንሰራለን”

“ሌሎች ቡድኖችም እዚህ መጥተው ለማሸነፍ የሚቸገሩ ይመስለኛል”  ጆን ስቴዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ 

ሰለ ጨዋታው….

“ሲዳማ እስካሁን ያልተሸነፈ ጥሩ ቡድን በመሆኑ ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ገምተን ነበር። ጨዋታው ከሜዳ ውጪ በሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የተደረገ በመሆኑም የተለየ ነበር ፤ ሌሎች ቡድኖችም እዚህ መጥተው ለማሸነፍ የሚቸገሩ ይመስለኛል”

የሽንፈቱ ምክንያት…

“ችግር የሆነው ሁለተኛው ግብ ሲቆጠርብን ነው። አንድ ግብ ተቆጥሮብህ ሁሌም ዕድል ይኖርሀል። ከእረፍት መልስ አጨዋወታችንን በመጠኑ ለመቀየር ሞክረን ነበር። ለውጦች ሲደረጉ ደግሞ ቢያንስ አስር የመረጋጊያ እና ወደ ለውጡ የመግቢያ ደቂቃዎች ያስፈልጋሉ። ሆኖም በዛን ሰዓት ጎል ተቆጥሮብናል። ያገኘነውን ቅጣት ምት ወደ ሳጥን ውስጥ በመጣል በሲዳማ ላይ ጫና ማሳደር ሲገባን ያን ሳናደርግ ቀረን። ሆኖም በድጋሚ ኳስ ማሸነፍ ብንችልም አሁንም ወደ ሳጥኑ ማሻማት ሳንችል ቀረን ይህን ባለማድረጋችንም በመልሶ ማጥቃት ግብ አስተናግደናል። እግርኳስ ጨዋታን ለማሸነፍ እንደዚህ ልትጫወት አትችልም። ይህ በትምህርት ቤት ሜዳ ላይ የምትጫወተው ዓይነት እግር ኳስ እንጂ በዚህ ደረጃ የምትጫወተው አይደለም”